ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ህዝቡን እንዳማረረው የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ

በጎንደር ከተማ የሚስተዋሉትን የመልካም አስተዳደርና የልማት ችግሮች መንግስት በአፋጣኝ እንዲፈታላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ጠይቀዋል ።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም፣ የህዝብ ተሳትፎና የቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ከጎንደር ከተማ ህዝብ ጋር ትናንት ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት ምላሽ ህዝቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በመለየት በጥልቅ የተሃድሶ ንቅናቄ ለመፍታት የተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመድኃኔዓለም ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አሰፋ ክንዴ "በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋለው ሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባር ህዝቡን ምሬት ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፤ ችግሩን በማረም ለውጤት ጥረት ሲደረግ አልታየም" ብለዋል።

ችግር ያለባቸው ግለሰቦችና አባላት በየጊዜው ቢገመገሙም ተገቢ የሆነ የማስተካከያ ርምጃ እየተወሰደ እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

መንግስት ለልማት ትኩረት ቢሰጥም በአፈፃፀም ሰፊ ችግር መኖሩን ነው ያመለከቱት።

"የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁን ለተገኘው ሰላም አስተዋጽኦ ቢያደርግም ህዝቡ የጠየቃቸው መሰረታዊ ጥያቄዎችን በመፍታት በኩል ትኩረት የተሰጠ አይመስልም" ያሉት ደግሞ የከተማው ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ አባይ የሱፍ ናቸው።

የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በሚጠበቀው ደረጃ ላይ እንዳልሆነም  ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ትምክህተኝነትን ለአማራ ህዝብ መስጠት ተገቢነት ያለው አስተሳሰብ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ዓባይ ፣ "ትምክህትም ሆነ ጠባብ በየትኛውም ብሄር በግለሰብ ደረጃ የሚገለጽ እንጂ እንደ ህዝብ መፈረጅ ተገቢነት የለውም" ሲሉ አስገንዝበዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የአዘዞ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወጣት ወረቀት ነጋ እንዳለው የመብራት መቆራረጥና የመሰረተ ልማት ጥራት መጓደል ህዝቡን ለእንግልት እየደረጋው ነው።

ለወጣቱ የተሰጠው ትኩረት በሚፈለገው ደረጃ ባለመሆኑ ለአደንዛዥ እፅ እየተጋለጠ መሆኑን ጠቁሞ፤ ችግሩ አሳሳቢ ቢሆንም መፍትሄ እየተወሰደ አለመሆኑን አመልክቷል።

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ ንጹሀንና ያልበደሉ እየታሳሩ ነው፤ የታሰሩት ለምን አይፈቱም? የሚሉና ሌሎች ተያያዝ ጥያቄዎችም በሌሎች የውይይቱ ተሳታፊዎች በመድረኩ ላይ ተነስተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ህዝቡ በየደረጃው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች እየተካሄደ ከሚገኘው ጥልቅ ተሃድሶ ጋር በማያያዝ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"በጥልቅ የተሃድሶ መድረኮች ችግሮቹ ተለይተዋል፤ ምንጩም ታውቋል፤ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የተቀመጡ በመሆናቸው ችግሮችን ፈጥኖ ለማረም የህዝቡ የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ ያስፈልጋል" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል ።

ባለፉት ጊዜያት በጎንደርና አካባቢው ተከስቶ የነበረውን ችግር በማርገብ ሰላምን ለማምጣት በተደረገው ርብርብ የህዝቡ ተሳፎ ወሳኝ እንደነበር ጠቁመው፤ በዚህም "ለጎንደርና አካባቢው ህዝብ መንግስት አክብሮቱን ያቀርባል" ብለዋል።

ችግሮቹ ዳግም እንዳይከሰቱ ህዝቡ አመራሩንና የድርጅት አባላትን ተከታትሎ ለማረምና ለማስተካከል በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ከወሰን ማስከበር ጋር ለተነሳው ጥያቄም "የሁለቱ ክልሎች ያላቸው ዘመን ተሻጋሪ መተሳሰብና ታሪካዊ ዳራ ጋር ተያይዞ የህዝቦቹን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የማንነት ጥያቄውም የዜጎች መተማመኛ የሆነውን ህገ መንግስት መሰረት በማድረግ የሚስተናገድ መሆኑን አቶ ደመቀ አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው፣ በአዋጁ ሰበብ ንጹሃን እየታሰሩ ነው ለሚባለው ከሚሊሻ ጀምሮ ባለድርሻ አካላት ላይ የተጠናከረ ግምገማ በማካሄድ የማስተካከያ ሥራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

"ያለአግባብ የታሰሩትን ማስረጃ ታይቶ እየተለቀቁ መሆኑንና በቀጣይም ተመሳሳይ ችግር ካለ እየታየ የሚፈቱበት ሁኔታ ይኖራል" ብለዋል።

ከወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄም የክልሉ መንግስት ከ800 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በጀት መመደቡንና የፌደራል መንግስትም ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

አቶ ገዱ እንዳሉት፣ ከመብራት መቆራረጥና ከመሰረተ ልማት ጥራት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ የክልሉ መንግስት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ይሰራል።

በህዝባዊ የውይይት መድረኩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች፣ መሳተፋቸውን ኢዜአ ገልጿል።