ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን በፀጥታ፣ በድንበር ቁጥጥር እና በመንገድ ዘርፍ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር በብሄራዊ ቤተመንግስት ተወያይተዋል።
መሪዎቹ በሁለትዮሽ፣ ቀጠናዊ እና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ሁለቱ ሀገራት ተቀራርበው መስራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
በፀጥታ፣ በድንበር ቁጥጥር እና በመንገድ መሰረተ ልማት በጋራ መስራት የሚያስችሉ የመግባቢያ ሰነዶችም ተፈርመዋል።
ሁለቱ ሀገራት አንዱ የሌላውን ሀገር ታጣቂ ቡድኖችን እንዳያስተናግዱ የሚያደርግ ስምምነትም ተፈራርመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በሀይል፣ ነዳጅ አቅርቦት፣ በጤና እንዲሁም በሚዲያ እና ኢንፎርሜሽን ዘርፎች በጋራ ለመስራት ከስምምነት ደርሰዋል።
ሀገራቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ሁለት ሀገር አቋራጭ መንገዶችን ለመገንባትም ተስማምተዋል።
መንገዶቹ በሁለቱ ሀገራት መካክጨከል የሚገኙ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን እርስ በርስ በመጠቀም ሁለቱም ሀገራት በጋራ ሊለሙ የሚችሉበትን መንገድ ያጠናክራሉ ተብሏል።
በሌላ በኩል ደቡብ ሱዳን በቀን እስከ 100 ሺህ በርሚል ነዳጅ የሚያጣራ መሰረተ ልማት እንደምታቋቁም ተገልጿል።
ከሚገነቡት መንገዶች መካከልም የነዳጅ ምርትን ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ የሚያስችል ይገኝበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማሳደግ ቋሚነት ያለውና በአመት ሁለት ጊዜ በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረግ የውይይት መድረክ እንዲኖር ከስምምነት መደረሱን ገልፀዋል። (ምንጭ፤ ኤፍ ቢ ሲ)