የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ረቂቅ ደንብ በቀጣይ ሳምንትም ውይይት እንደሚደረግበት ተገለጸ

በአገር አቀፍ ደረጃ  የሚገኙ 22 የፖለቲካ ፓርቲዎች  በፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር ረቂቅ ደንብ ላይ ሲያካሄዱት የነበረው ውይይት ባለመጠናቀቁ  ቀጣይ ሳምንት ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግበት ተገለጸ ።   

ከሰባት የፖለቲካ  ፓርቲዎች  የተውጣጡ  አባላት የያዘው  ኮሚቴ በእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ የቀረበውን  የቅድመ ውይይት ሰነድ አንድ ላይ በማቀናጀት  ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርቧል ።

ፓርቲዎቹ በዛሬው እለት ባካሄዱት ውይይት የቀረበው የተቀናጀ ረቂቅ ደንብ ከተነበበላቸው በኋላ  ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች  አስተያየት እንዲሰጡበት ተደርጓል ።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች  በረቂቅ ደንቡ ላይ ከአባሎቻቸው  ጋር  ለመመክር እንደሚፈልጉ በመግለጻቸው በቀጣይ ሳምንት ለመገናኘት ተስማምተዋል ።

በመጪው ሳምንት በረቂቅ ደንቡ በዝርዝር በቀረቡ 12 ነጥቦች ላይ በፓርቲ ደረጃ ተነጋግረው የየራሳቸውን አቋም ይዘው ለመቅረብ 22ቱም ፓርቲዎች ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ በቀጣይ ሳምንት አርብ በሚያካሂዱት ውይይት ረቂቅ ደንቡን ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።