121ኛው የአድዋ ድል በዓል ህዳሲያችንን ለማረጋገጥ ቃል የሚንገባበት ዕለት ነው፤ መ/ ኮ/ጉ/ጽ/ቤት

የዘንድሮው 121ኛው የአድዋ ድል በዓል በአገሪቱ የተቀጣጠለውን የህዳሴ ጉዞ ዳር ለማድረስ  የተጀመረውን የጸረድህነት ትግል በማጠናከር ቀጣይነት ያለው ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ እጅና ጓንት ሆነን በመስራት ታሪክን ለመድገም ቃል የሚገባበት እለት እንደሚሆን  የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ጽህፈት ቤቱ በሳምንታዊ የአቋም መግለጫው እንዳስታወቀው  የዓድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ምክንያት እንደሆነ ሁሉ  ኢትዮጵያ እየተከተለች ያለው   ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመርም ለሌች የአፍሪካ አገራት ተምሳሌት ይሆናል ብሏል።

ወጣቱ ትውልድ ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ለሀገር ክብርና ለሰንደቅ ዓላማ  በጋራ የመቆም እሴት በመጠበቅ የኢትዮጵያዊያንን  አንገት አስደፍቶ ለዘመናት የዘለቀው  ድህነት ላይ በጋራ በመረባረብ  አንጸባራቂ ድሎች እያስመዘገበ እንደሚገኝና ይህንን አጠናክሮ እንደሚቀጥል   መግለጫው ጠቁሟል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ነው

በኢፌድሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ (የካቲት 17 ቀን 2009 ዓ.ም)

ይህ ትውልድ፡ ድህነትን ለማሸነፍ በጀመረው ትግል አንጸባራቂውን የአድዋ ድል እየደገመ ነው!

አያት ቅድመ አያቶቻችን ወራሪውን የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር  ድል ያደረጉበት የአድዋ ድል በዓል ዘንድሮ ለ121ኛ ጊዜ የፊታችን የካቲት 23 ቀን ይከበራል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ዘመናዊ ጦር የታጠቀውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር የኢትዮጵያ ጀግኖች በኋላ ቀር የጦር መሳሪያዎች ያሸነፉበት ድል በወራሪ ነጮች ላይ የተገኘ የመጀመሪያው የጥቁር ሕዝቦች ድል ነበር፡፡ ጥቁር ሕዝቦች በባርነት እና በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ይማቅቁ በነበረበት በዚያ አስከፊ ዘመን የተገኘው ይህ ድል ከአፍሪካም አልፎ የመላው ጭቁን ሕዝቦች አንጸባራቂ ድል እና የኩራት ምንጭ ለመሆን የበቃ ጉልህ የታሪካችን አካል ነው፡፡

ከድሉ በኋላም የአፍሪካ ቅኝ ገዢ ሀገራት ከሀገራችን ጋር ለድርድር እንዲቀመጡ ያስገደደ፣ የወቅቱ ኃያላን ሀገራት በመዲናችን በመሰባሰብ ለዲፕሎማሲያዊና ለንግድ ግንኙነት እርስ በእርስ እንዲሽቀዳደሙ ያደረገ ክስተትም ነበር፡፡ በቅኝ ግዛት ተሸማቀው የነበሩ አፍሪካዊያን ተጭኖባቸው በነበረው የበታችነት መንፈስ ላይ እንዲያምፁ የገፋፋ፣ ለትግል ያነሳሳና ቆይቶም ለመላው አፍሪካ አንድነት (ለፓን አፍሪካ) እንቅስቃሴ መመሥረት ምክንያት የሆነ ድል ነበር፡፡

የዛሬው ትውልድም በማሽቆልቆል ጉዞ ላይ የነበረችውን ሀገሩን ለመታደግ፡ በህዳሴ ጉዞው ውስጥ ታላቅ ድልን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡  ድህነትን በመጋፈጥ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ እየተረጋገጠ የሚገኘው ይህ ድል  የአሁኑ ትውልድ ለአገሩ ክብር ያለው ቀናዒነት ውጤት ነው። ዛሬ በራሳችን አቅም ተዓምር የሚባሉ ፕሮጀክቶችን ሠርተን ማጠናቀቅ እንደምንችል እያስመሰከርን ነው። ለዘመናት አይደፈርም ሲባል የቆየውንና በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚጠይቀውን ታላቁ የኢትዮጲያ ህዳሴ ግድብን በራሳችን አቅም መገንባት መቻላችን የዚህ ማሳያ ነው፡፡

የዓድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ምክንያት እንደነበረ ሁሉ፡ አገራችን አሁን እየተከተለችው ያለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት አፍሪካ በራሷ ፖሊሲ ማደግ እንደምትችል እያሳየ ነው። የዓድዋ ድል የጥቁር ህዝቦች መኩሪያ እንደሆነው ሁሉ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትከተላቸው ፖሊሲዎች የድሃ ሕዝቦች አለኝታ በመሆን ላይ ናቸው። አፍሪካን ከድህነት ለማውጣት፣ አህጉሪቱ የራሷን ጉዳይ በራሷ እንድትፈታ ለማስቻል ሀገራችን ግንባር ቀደም  ሚና እየተጫወተች ትገኛለች። የአየር ንብረት ለውጥን በመሣሠሉ ታላላቅ ጉዳዮች ዙሪያም የአፍሪካ ህዝቦችን መወከል ችላለች።

 

በአጠቃላይ የአሁኑ ትውልድ ከአያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን ለሀገር ክብር በጋራ የመቆም እሴት በዘላቂ መሠረት ላይ በማጽናት ለዘመናት አንገታችንን አስደፍቶን በኖረው ድህነት ላይ በከፈተው ዘመቻ ከወዲሁ አንጸባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ ይገኛል።

 

የኢፌዴሪ መንግስት ለኢትዮጲያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንኳን ለ121ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ እያለ የተጀመረው የህዳሴ ጉዞ ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ የአሸናፊነት ምልክትና ቅርስ እንደሚሆን ያለውን ጽኑ ዕምነት በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በዓሉን ስናከብር፡ በጀመርነው የህዳሴ ጉዞ ድህነትን በማሸነፍ የአባቶቻችንን ታሪክ ለመድገም ቃላችንን የምናድስበት እንዲሆን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡