የጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ባለፉት ሁለት ቀናት ባደረገዉ መደበኛ ጉባኤ በቅርቡ በክልሉ የተካሄደዉን ጥልቅ ተሃድሶ ተከትሎ ከስልጣን የተነሱ አመራሮችን ለመተካት የቀረቡ አዳዲስ ሹመቶችን ማፅደቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ፡፡
የቢሮዉ ሃላፊ አቶ ዑሞድ ኦታዎ ዑማን ለዋልታ እንደተናገሩት የክልሉ ምክር ቤት በሃሰት የትምህርት ማስረጃ ተጠርጥረዉ ከስልጣናቸዉ የተነሱት የተለያዩ ቢሮዎች ሃላፊዎች በአዳዲስ ተሿሚዎች ተተክተዋል፡፡
ጉባኤዉ በቅርቡ በክልሉ በተከሰተዉ አለመረጋጋት ወቅት በሁለት ግለሰቦች ግድያ ላይ በመሳተፍ የተጠረጠሩ ባለስልጣናት ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ መወሰኑንም አመልክተዋል፡፡
በምክር ቤቱ ዉሳኔ መሰረት የመንግስት ኮሚኒኬሽን፣ የቴክኒክና ሞያ ፣የሰዉ ሃብት፣ የንግድ፣ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ እንዲሁም ሌሎች ቢሮዎች ሃላፊዎች በአዳዲስ ተሿሚዎች እንዲተኩ መደረጉን የቢሮ ሃላፊዉ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈንና የፀረ-ሰላም ሃይሎችን እንቅስቃሴ ለመከላከል ከሁሉም የክልሉ ቀበሌዎች የተዉጣጡ ታጣቂዎችን በማስልጠን ለማሰማራት ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ክልሉ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር ድንበር በሚዋሰንባቸዉ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችንና እንስሳትን ደህንነት ለመጠበቅ የመከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ልዩ ሃይል ጋር በመተባበር ዉጤታማ ስራ እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የጋምቤላ ክልል በጎረቤት ደቡብ ሱዳን የተቀሰቀሰዉን የእርስ በርስ ግጭት ተከትሎ ከፍተኛ የሆነ የስደተኞች ቁጥር እያስተናገደ መሆኑንና የክልሉ መንግስትም ይህን ከግምት ዉስጥ በማስገባት ስደተኞቹ ተገቢዉን ድጋፍ የሚያገኙበትንና በሚኖሩበት አካባቢ ምንም አይነት የሰላም ስጋት እንዳይፈጠር የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሁኑን አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ በክልሉ የመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ ናቸዉ በሚል የተለዩ ማነቆዎች በመቅረፍ ላይ ያተኮረ ስራ በክልሉ እንዲከናወን አቅጣጫ ማስቀመጡንና የዚህ አፈጻጸምም ከስድስት ወር በሚካሄደዉ ጉባኤ በጥልቅ ለመገምገም እቅድ መያዙ ተመልክቷል፡፡