ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ትናንት በተከበረው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ( ማርች 8) ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት በግንባታ ላይ የሚገኘውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ የሴቶች የድጋፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል ።
ትናንት በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ 2ሺ 500 ተወካይ ሴቶችን ባወያዩበት ወቅት አቶ ኃይለማርያም እንደገለጹት ማርች 8 ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች መራራ ትግል በማድረግ በሚደርሱባቸው የተለያዩ ፖለቲካዊ ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጭቆናዎች ላይ ድል መቀናጀታቸውን የሚያስታውስ ቀን ነው ብለዋል ።
ሴቶች ለእኩልነትና ለዴሞክራሲ መከበር ከባድ መስዋትነት በመክፈል ጭቆናን ለማስወገድ ታሪካዊ ትግል ማካሄዳቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስረድተዋል ።
በአሁኑ ወቅት ሴቶች ከቀደሙት ሴቶች በተለየ ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ጥቅሞቻቸውና መብቶቻቸው በመከበራቸው ምክንያት በአገሪቱ በተመዘገቡት የፖለቲካዊና ማህበራዊ ለውጦች ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ጠቅላይ ሚንስትሩ ተናግረዋል ።
ሴቶች ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ነጻነታቸውን ይበልጥ በማስከበር በራሳቸው ብርቱ እንቅስቃሴ በማድረግ ለአገሪቱ ጠቅላላ ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል ።
እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለጻ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማሳደግ የሴቶች የቁጠባ ባህልን ከማሳደጉም በላይ ለአገር ኢኮኖሚ ገንቢ ሚና ይጫወታል ።
በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት የተካሄደው ውይይት ከተጠናቀቀ በኋላ ባለፉት ሦስት ወራት በቁጠባ የተሻለ አፈጻጻም ያስመዘገቡ ሴቶች ከጠቅላይ ሚንስትሩ ሽልማት ተበክቶላቸዋል ።
በመጨረሻም ተወካይ ሴቶቹ ለጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም የተለያዩ ጥያቄዎችን በማቅረብ ምላሽ ተሠጥቷቸዋል ።
የዘንድሮ 41ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “ህዳሴያችንን ለማረጋጋጥ ሴቶች በቁጠባ ላይ የጀመሩትን ሥራ አጎልብተው መቀጠል አለባቸው ” በሚል መሪ ቃል ተከብሯል ።