የሀገሪቱ ግብርና በማዘመን የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግር ማፋጠን እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ኮሙሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት አስገነዘበ ፡፡
ስምንተኛው ሀገር አቀፍ የአርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች በዓል ከመጋቢት 1 ቀን 2009 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ለሦስት ቀናት በአዳማ ከተማ በደማቅ ስነ-ሥርዓት በመከበር ላይ ይገኛል።
የበዓሉ ዋና ዓላማ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ አርሶ አደሮችንና ከፊል አርብቶ አደሮችን በማበረታታት ወደ ባለሀብትነትና ወደ ኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ እንዲሸጋገሩ ማትጋት ነው ብሏል ፡፡
መግለጫው እንዳመለከተው ፤በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና ዘመናዊ የግብርና አሠራሮች የግብርና ምርታማነታቸውን በማሳደግ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ሞዴል አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣የልማት ሠራተኞች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም ባለሃብቶችና ልዩ ልዩ ተቋማት ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እጅ ሽልማቶቻቸውን ይቀበላሉ።
የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት በአግባቡ በመጠቀም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ወይም ጥሪት ያፈሩ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ወደ ባለሃብትነት የሚሸጋገሩበት ዕለት በመሆኑም በዓሉ ትልቅ ግምት የሚሰጠው መሆኑን አስረድተዋል ።
ከተሸላሚዎቹ መካከል ሴቶች እና ወጣቶች የሚገኙበት መሆኑም ታላቅ ግምት የሚሰጠው ነው ብሏል ፡፡
ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉና ዕሴት ወደ ሚጨምሩ የተለያዩ የግብርና ልማት ኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች የተሸጋገሩ፣ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል የፈጠሩ ባለሃብቶችም የልማት አርበኞች መሆናቸውን አንስቷል ።
በየዓመቱ ምርትና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ፣ ኑሯቸውን እያሻሻሉና ሃብት እያፈሩ ወደባለሃብትነት የሚሸጋገሩ የልማት ጀግኖች መሆናቸውን ገልጿል ፡፡
በአነስተኛ አርሶ አደሮቻችንና አርብቶ አደሮቻችን እጅ ሃብት እየተፈጠረ መሄዱ እና ወደ ባለሀብትነት በሂደትም ወደኢንዱስትሪ የሚያደርጉት ሽግግር የነገ መዳረሻ ከወዲሁ የሚያሳይመሆን አስገንዝቧል ፡፡
መግለጫው በመላ ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደረገውን ሽግግር ለማሳካት ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አርቧል ፡፡