የአማራ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን፣ ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ጀመረ።
ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶች በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ስለመፈጸማቸው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚገመግም ተመልክቷል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ምክር ቤቱ የአስፈጻሚ አካሉን የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በማዳመጥ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል።
ለአስፈጻሚ አካሉና ለዳኝነት ዘርፉ የሚመደበው በጀት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በመከታተል ያረጋግጣል።
ችግር ካለም በክትትልና ቁጥጥር አሰራሩ የእርምት እርምጃ ይወስዳል።
የመንግስት ተቋማት በሕብረተሰቡ ዘንድ እርካታ ለመፍጠርና ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የተፋጠነ ምላሽ ለመስጠት የተሃድሶ ንቅናቄ ማካሄዳቸውን አስታውሰዋል።
በእዚህ ጉባኤም ከተሃድሶው ማግስት የመጡ ለውጦችና የተገኙ መልካም ልምዶች ከዋና ዋና ተግባራት ጋር ተያይዘው እንደሚገመገሙም ጠቁመዋል።
በተጨማሪም "ያለፉት ስድስት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅድ አፈጻጸም በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት እየተመራ ስለመሆኑ ጉባኤው ትኩረት ሰጥቶ ይመክርበታል" ብለዋል አፈ ጉባኤው።
በስድስት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተቋማት ሪፖርት ቀድሞ እንዲታይ ከመደረጉም በላይ እስከ ቀበሌ ድረስ በተካሄደ የመስክ ምልከታ የተስተዋሉ ችግሮች፣ መልካም ተሞክሮዎችና ስኬቶች ተለይተው ለጉባኤው እንዲቀርቡ ይደረጋል።
አቶ ይርሳው እንዳሉት፣ የምክር ቤቱ አባላት ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ወደ መረጣቸው ሕዝብ ሄደው በተለያዩ መድረኮች ከ113 ሺህ 400 በላይ ነዋሪዎች የተሳተፉበት ውይይት በማካሄድ ግብዓት ተሰብስቧል።
የተነሱ ችግሮች በየደረጃው ትኩረት እንዲሰጥባቸውም ከሦስት ሺህ 600 በላይ አመራሮች ጋር በመምከር አመራሩ መፍታት የሚችለውን ኃላፊነት እንዲወስድና ከአቅም በላይ የሆኑት የጋራ አቅጣጫ እንዲቀመጥባቸው መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ይርሳው እንዳሉት ጉባኤው የክልሉ ሕዝብ የልማት ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ በመጣበት ማግስት መካሄዱ ልዩ ያደርገዋል።
ምክር ቤቱ ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ከአስፈጻሚ አካሉ ሪፖርት ባሻገር የዳኝነት አካሉና የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች ሪፖርት ቀርቦ እንደሚመከርበት ለማወቅ ተችሏል።
በተጨማሪም ጉባኤው የተለያዩ አዋጆችን፣ ውሳኔዎችንና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።