በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር ከቀረቡት አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 12ቱ ለብቻቸው ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ከስምምነት ሳይደርሱ ተለያዩ።
ከኢህአዴግ ውጭ በድርድሩ ሂደት ዙሪያ ለመወያየት ቀነ ቀጠሮ ከያዙት 21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መድረክን ጨምሮ ዘጠኙ ፓርቲዎች ባልታወቀ ምክንያት በቀጠሯቸው እንዳልተገኙ ነው የተገለጸው።
ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር አስፈላጊና መሰረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለመደራደር የሚያስችል ረቂቅ ሰነድ ለማዘጋጀት በጋራ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
እስካሁን በተደረጉ ውይይቶች በመደራደሪያ ረቂቅ ሰነዱ ዓላማ ላይ ከስምምነት ቢደርሱም በሰነዱ ስያሜ እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መስማማት ተስኗቸው ቆይተዋል።
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር መደራደር የሚችሉት ፓርቲዎቹ በተናጠል የየራሳቸውን የመደራደሪያ አጀንዳ በማቅረብ፣ 21ዱ ፓርቲዎች በጋራ ተስማምተው የጋራ አጀንዳ በመቅረፅ እንዲሁም "የራሴ ለየት ያለ አጀንዳ አለኝ" የሚል የፖለቲካ ፓርቲ በግል በሚያቀርበው የመደራደሪያ ሃሳብ በሚሉ ሶስት መንገዶች ነው።
በመሆኑም 21ዱ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር "በቅንጅት ወይስ በተናጠል" በሚለው ላይ ሁሉም ፓርቲዎች ባሉበት መስማማት ባለመቻላቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻቸውን ተወያይተው ስምምነት ላይ ለመድረስ ዛሬ በቀጠሮ ተገናኝተዋል።
የተገኙት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ሳይሟሉ ተስማምቶ ውሳኔ ላይ መድረስ ስለማይችሉ አብዛኞቹ በተናጠል ጥቂቶቹ አንድነት ፈጥሮ በመደራደር፤ የመላው ኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኦህዴፓ) ደግሞ ከሁለቱም ሳይመርጥ የየራሳቸውን አቋም አቅርበው ሳይስማሙ ተለያየተዋል።
ፓርቲዎቹ በቀጣይ መጋቢት 9 ቀን 2009 ዓ.ም ኢህአዴግን ጨምሮ በሚገናኙበት ዕለት ሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተነጋግረው መስማማት ከቻሉ አንድነት ፈጥረው መስማማት ካልቻሉ ደግሞ በተናጠል ለመደራደር ቀነ ቀጠሮ ይዘዋል-(ኢዜአ)።