በአማራ ክልል ባለፉት 6 ዓመታት ከአንድ ቢሊዮን 25 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ ግዥ መፈጸሙን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበትን 6ኛ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር እየተዘጋጀ የሚገኘዉ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽ/ቤት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ይርሳው የአማራ ክልል ህዝብ የግድቡን ግንባታ ለማስቀጠል በገንዘቡ ፣በጉልበቱና በዕውቀቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በክልል ደረጃ 1 ቢሊዮን 25 ሚሊዮን 885 ሺህ 224 ብር ቦንድ ግዥ እንደተፈጸመ የገለጹት አቶ ጌትነት ከዚህ ውስጥ የመንግስት ሰራተኛው 462 ነጥብ 9 ሚሊዮን፣ባለሃብቱና የንግዱ ማህበረሰብ 85 ነጥብ 1 ሚሊዮን፣የክልሉ አርሶ አደር 211 ነጥብ 9 ሚሊዮን እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ 258 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ማካሄዳቸዉን ተናግረዋል፡፡
በልገሳ መልክም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡የክልሉ አርሶ አደርም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከደለል ለመከላከል የሚያስችልና 18 ቢሊዮን ብር የሚገመት የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ጌትነት አክለውም በዚህ ዓመት በዓሉን ለማክብር ከየካቲት 20 እስከ 29/2009 ዓ.ም በተካሄደው የቦንድ ግዥ ሳምንት 16 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ እንደተፈጸመ ገልጸው በዓሉን መጋቢት 24/2009 በልዩ ልዩ ሁነቶች በድምቀት ለማከበር በቂ ዝግጅት መደረጉን አመልክተዋል፡፡
“የታላቁ የኢትዮጵ ህዳሴ ግድብ የአንድነታችን ህብረ ዜማ የህዳሴያችን ማማ ነው!” በሚል መሪ መዕክት እንደሚከበር የገለጹት አቶ ጌትነት የክልሉ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለህዳሴው ግድብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡