ተሃድሶውን ዉጤታማ ለማድረግ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ማሻሻል እንደሚገባ ምክር ቤቱ አስታወቀ

የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ክልላዊ  መስተዳድር ምክር ቤት የክልሉን ሴክተሮች ያለፉት ሁለት ወራት የካፒታል ፕሮጀክቶች የማካካሻ እቅድ አፈጻጸም በመገምገም አቅጣጫ ባስቀመጠበት ወቅት ጥልቅ ተሃድሶዉን እዉን ለማድረግ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ማሻሻል እንደሚገባ አስታዉቋል፡፡

ምክር ቤቱ የልዩ ልዩ ሴክተሮችን የካፒታል ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የማካካሻ እቅድና ያለፉት ሁለት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርትን በመገምገም ዝርዝር ውይይት ያደረገ ሲሆን በርካታ መዋዕለ ንዋይ የሚመደብለትን የካፒታል ፕሮጀክት በልዩ ሁኔታ በመስተዳድር ምክር ቤት የመገምገም ንቅናቄ ውጤት እያመጣ መሆኑን ባወጣዉ መግለጫ አመልክቷል፡፡

ንቅናቄው ከተጀመረ በኋላ ያለው አፈጻጸም ሲታይም ወደ ትክክለኛው መስመር ለመግባት ጥሩ ጅማሬ መሆኑን የሚያመላክት እንደሆነ መስተዳድር ምክር ቤቱ መገምገም ችሏል፡፡

የምክር ቤቱ ውይይት የተጀመረውን ንቅናቄ በተሻለ ውጤት በማጀብ ለማስቀጠል በዋናነት ማነቆዎች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነዚህን አንኳር ማነቆዎች በመለየት ችግሮቹን ለመቀረፍና ለቀጣይ ወራት አፈጻጻም የሚረዱ አቅጣጫዎችን እንዳስቀመጠ በመግለጫ ተጠቁሟል፡፡

ለካፒታል ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆን ቁልፉ ችግር የማስፈጸም አቅም ውስንነት መሆኑን የገመገመው መስተዳድር ምክር ቤቱ ይህም ችግር ከአመራሩ አመለካከት፣ዝግጁነትና አቅም ማነስ እንዲሁም ከክትትልና ድጋፍ አለመጠናከር ጋር የሚያያዝ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡

 ፕሮጀክቶች በሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት የማይመሩ በመሆኑ የሚጠበቀውን ውጤት በተያዘለት ጊዜና ጥራት ማምጣት እንዳልተቻለ ምክር ቤቱ በትኩረት የገመገመ ሲሆን በቀጣይ ይህን የቅንጅት ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚያስፈልግ አስምሮበታል፡፡

የግንባታም ሆኑ ሌሎች ፕሮጀክቶች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ታስበው የሚጀመሩ ቢሆንም በአፈጻጸም ጉድለት ምክንያት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆነው እየቀረቡ መሆኑን በአጽንኦት ያስቀመጠው የደቡብ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት የፕሮጀክት አስተዳደርን በማሻሻልና በማጠናከር የህዝቡን እርካታና ተጠቃሚነት የበለጠ ማረጋገጥ እንዲቻል የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

መስተዳድር ምክር ቤቱ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የፊዚካል ስራው በተጀመረበት ክትትል ልክ ፋይናንሺያል ስራውንም መከታተል እንደሚገባ፣ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ከማጠናቀቅ ባሻገር በጥራት እንዲጠናቀቁ በማድረግ በኩል ትኩረት እንደሚሻ ለኮንትራክተሮች የሚፈጸሙ ክፍያዎች ከሰኔ አጋማሽ በፊት መጠናቀቅ እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡
 

በ2010 እንዲጀመሩ የሚታሰቡ ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ስራዎች በአስቸኳይ መሰራት እንደሚገባቸውና  ከተጫራቾች ጋር የሚገቡ የግንባታና ሌሎች ውሎች የመንግስትን ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ እንዲፈጸሙም  አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በመጨረሻም የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ በጥልቅ ተሃድሶው የተገባውን ቃል በተግባር ለመመለስ አንዱ መንገድ የካፒታል ፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ማሻሻል በመሆኑ ሁሉም በቅንጅትና በትጋት በመስራት የህዝቡን ሙሉ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት አሳስቧል፡፡