በሁከቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 5ሺህ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በህግ እየተስተናገደ  ነው -ቦርዱ

በሁከትና ብጥብጥ የተሳተፉ 5 ሺህ የሚጠጉ ተጠርጣሪዎችን ተለይተው ጉዳያቸው በህግ አግባብእየተስናገደ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ አስታወቀ።

የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ የክትትልና ቁጥጥር ሪፖርታቸውን ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንደገለጹት ፤በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ ላይ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ 26 ሺህ 130 ተጠርጣሪዎች ናቸው፡፡

ከነዚህም 20 ሺህ 659 ተጠርጣሪዎች ተሃድሶ ወስደው መለቀቃቸውን አስታውቋል፡፡

ቦርዱ በተሃድሶ የተመለሱት ታራሚዎች አይደገምም በሚል መፈክር ያወደሟቸውን ተቋማት መልሰው በመገንባት ላይ እንደሚገኙም በመጥቀስ ፡፡

ሌሎች 4 ሺህ 996 ደግሞ ለህግ የሚቀርቡ ሆነው በመለየታቸው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ነው ያመለከቱት ፡፡

የመርማሪ ቦርዱ ሰብሳቢ 475 ተጠርጣሪዎች ግን እንደተያዙ በወቅቱ በምክር ተለቀዋል ብሏል ።

ቦርዱ በሪፖርቱ ተጠርጣሪዎችን ከማሰር ይልቅ ታርመው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉ ለሰላምና መረጋጋቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ መፍጠሩን አስረድቷል።

ልዩ ትኩረት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ከምግብ አቅርቦትና ከህክምና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ እንዲደረግ፣ የመረጃ አያያዝና ልውውጥ ስርዓቱን ማጠናከርና ወደማዕከላቱ የሚላኩ ተጠርጣሪዎችን ከማዕከላቱ የመያዝ አቅም ጋር የተጣጣመ ማድረግ በቀጣይ ሊስተካከሉ እንደሚገባም አስገንዝቧል ፡፡

ቦርዱ ተጠርጣሪዎችን መለየት፣ ማሳወቅና የሚቆዩበት ስፍራን ተመልክቶ መስተካከል ያለባቸውን እንዲስተካከሉ ነው ያሳሰበው ።

በዚህም በሁለት ዙር በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር በመጀመሪያው ዙር ከነበሩት ችግሮች በሁለተኛው ዙር በርካታ መስተካከሎች መደረጉን አስረድቷል ።

በቂም በቀል የተያዙና ተሸፋፍነው የታለፉ ተጠርጣሪዎች ላይ ማጣራት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሰብሳቢው ፤ በሂደቱ ያሉ ችግሮችን በማጥራት ተጠያቂ የሚሆኑበት አሰራር መኖሩንም በምላሹ ጠቁሟል ፡፡

በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፎ ከተጠረጠሩት በስተቀር የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው የታሰሩ ሰዎች አለመኖራቸው መረጋገጡን ገልጸዋል።

ከአንዳንድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎቻችን 'የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አባል በመሆናቸው ብቻ ተይዘው እንግልት ዶርሶባቸዋል' የሚል አቤቱታ እንደቀረበለትም ጠቅሷል።

አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ያቀረቡትን አቤቱታ በመያዝ እስረኞች በሚገኙበት ስፍራ ተገኝቶ የማጣራት ሥራ ማከናወኑን አስረድተዋል ።

በምርመራና ማጣራት ስራው በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል ተብለው ተጠርጥረው ከታሰሩ በስተቀር የተቃዋሚ ፓርቲ አባል በመሆናቸው የታሰሩ እንደሌሉ ቦርዱ ማረጋገጡን ነው ያብራሩት ።

በአጠቃላይ በሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው የታሰሩትም ቢሆኑ የደረሰባቸው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንደሌለ ቦርዱ አረጋግጧል" ብለዋል።

በተጨማሪ የተጠርጣሪዎች በጠባብ ክፍሎች መታሰር፣ የመጠየቂያ ጊዜ፣ የእስረኞች ለፍርድ  ሳይቀርቡ ለወራት መቆየትና በዋስትና ተለቀን መልሰው አሰሩን" የሚሉ አቤቱታዎችና ጥያቄዎች ለኮማንድ ፖስቱ ቀርበው መፍትሄ እንደተሰጣቸው አቶ ታደሰ ገልጸዋል።

ቦርዱ ከቀረቡለት 174 አቤቱታዎች፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶች 54ቱ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸው አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ማስተላለፉን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ 120 አቤቱታዎችና ጥቆማዎች ለክትትልና ቁጥጥር ስራው በግብዓትነት ጥቅም ላይ መዋላቸውንም አስረድተዋል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የማይያያዙ አቤቱታዎች፣ ጥቆማዎችና አስተያየቶችን ያቀረቡ ዜጎች ጉዳዮቹን በመደበኛ አሰራር እንዲያስፈፅሙ ምክር ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል ።

በሌላ በኩል ፀረ-ሰላም ኃይሎች አሁንም "በህቡዕ በመንቀሳቀስ ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ኮማንድ ፖስቱ በትኩረት ይከታተል" የሚሉ ጥቆማዎች እንደቀረቡለትም አስታውቀዋል።

በዚህ መሰረት ቦርዱ ኮማንዱ ፖስቱ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።

ህዝቡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካለው ጠቀሜታ አንጻር እንዲቀጥል ፍላጎት ማሳየቱን አመልክቷል ።

አለመራዘምምመንግስት የፊታችን ሐሙስ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ አስተያየትና ምላሽ ሲሰጥ ስለ አዋጁ መራዘምና  ማብራሪያ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።