ኢትዮጵያና ዛምቢያ የጋራ የትብብር ኮሚሽን መሰረቱ

ኢትዮጵያና ዛምቢያ በመካከላቸው የተደረሱ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተከታትሎ የሚያስፈጽም ቋሚ የጋራ የትብብር ኮሚሽን መሰረቱ።

ዛምቢያ ከአፍሪካ ህብረት፣ ከምስራቅና ደቡባዊ የአፍሪካ አገሮች የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እና ከደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የልማት ትብብር (ሳድክ) አባልነቷ ባሻገር በቀጣናው ቁልፍ ሚና ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች።

ባለፉት ሁለት ቀናትም በአገሪቷ መዲና ሉሳካ የሁለቱ አገሮች ቋሚ የጋራ የትብብር ኮሚሽን ስብሰባ ተካሂዷል።

ስብሰባው በሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተመራ ሲሆን፤ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መክሯል።

የውይይቱ አጀንዳዎች ያተኮሩት በአገሮቹ መካከል በተፈረሙ ስምምነቶች እና በቀጣይ በሚፈረሙ ሰነዶች ላይ ነበር።

ኮሚሽኑ ከሁለት ዓመታት በፊት በተደረሰ ስምምነት መሰረት የተቋቋመ ሲሆን፤ የአገሮቹን ግንኙነት ማሳደግና በመካከላቸው የተፈረሙ ስምምነቶችን ተከታትሎ ማስፈጸም ላይ አተኩሮ ይሰራል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በሉሳካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች በማሳደግ በኩል ኮሚሽኑ ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

"ዋና ዓላማው የአገራቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ይበልጥ ማጠናከር ነው” ያሉት ዶክተር ወርቅነህ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች በሚነሱ ጉዳዮች ላይ ጥቅሞቻቸውን መሰረት በማድረግ በጋራ እንደሚወሰንም ነው ያስረዱት።

የአገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃሪ ካላባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያና ዛምቢያ ያሏቸውን ሃብቶችና መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም ለዜጎቻቸው ተጠቃሚነት በጋራ መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።

ለዚህም ኮሚሽኑ በአገሮቹ መካከል የተደረሱ ስምምነቶችን ተፈጻሚነት በመከታተል የበኩሉን መወጣት እንደሚጠበቅበት ነው ያመለከቱት።

የሁለቱ አገሮች ቋሚ የጋራ የትብብር ኮሚሽን ቀጣይ ስብሰባውን ከሁለት ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ይጠበቃል ።

የትብብር ኮሚሽኑ የተመሰረተው ሁለቱ አገሮች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 ባሳለፉት ውሳኔ መሰረት ነው።

ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ግንኙነት ያላት ዛምቢያ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻ እንደወጣች ነበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1965 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁለቱ አገሮች በተለያዩ መስኮች በትብብር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን፤ በተለያዩ ጊዜያትም የትብብር ስምምነቶች ማድረጋቸው ይታወሳል-(ኢዜአ) ።