የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለአራት ወራት እንዲራዘም ወሰነ።
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባው የተገኙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ጸሐፊና የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ለምክር ቤቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም ያስፈለገበትን ምክንያት አቅርበዋል።
ምክርቤቱም የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ የወጣውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማደስ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሰፊ ውይይት አካሂዷል ።
ሚኒስትሩ የሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ተጨማሪ ጊዜ ማስፈለጉን ለአዋጁ መራዘም ማስፈለጉን አስታውቀዋል ።
እንደዚሁም በክልሎች አዋሳኞች በሚነሱ ችግሮች ለመጠቀም የሚፈልጉ ጸረ ሰላም ኃይሎች እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው፣ በሁከት እና ብጥብጡ ቀንደኛ መሪዎች ከነበሩት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቢያዙም ቀሪ በመኖራቸው እና በወረቀት ፅሁፎችን በመበተን አሁንም ሰላም እና መረጋጋትን ለማደፍረስ የሚጥሩ ወገኖች አልፎ አልፎ በመታየታቸው አዋጁን ማራዘም ማስፈለጉን ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
በአንዳንድ ከተሞች በጸጥታ ኃይሎችና በመሰረተ ልማቶች ላይ ፈንጂ በመጣል ሽብር ለመፍጠር የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው አዋጁ እንዲራዘም ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን ጨምረው አብራርተዋል ፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ዝውውር መኖሩና አልፎ አልፎ መንገድ በመዝጋት የዘረፋ ተግባር የሚፈጽሙ ኃይሎች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አለመዋላቸውም ሌላው ምክንያት መሆኑን ለምክርቤቱ አስገንዝበዋል ።
በሀገሪቱ በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት ህዝቡ የተሻለ ሰላም እንዲሰፍን አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት እንዳለውም አረጋግጠዋል ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መርማሪ ቦርድም በመላ ሀገሪቱ ያደረገውን ቅኝት መሰረት አድርጎ አዋጁ ቢራዘም የሚል አስተያየት ለምክር ቤቱ አቅርቧል ።
ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት እንዲራዘም በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ተከስቶ የነበረውን ሁከትና ብጥብጥ ተከትሎ በመደበኛው የህግ ስርዓት መቆጣጣር ባለመቻሉ መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ የሚታወቅ ነው ።