የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት በዓል "ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የሀገራችን ህብረ-ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ!" በሚል መሪ ቃል ነገ ቀን ጉባ ላይ ይከበራል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈትቤት ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ፤የዛሬ ስድስት ዓመት ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የቀረበውን ጥሪ በመቀበል መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ለግንባታው ስኬት ያደረጉት የገንዘብ፣ የጉልበት፤ የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ የዘመናችን ትልቁ ገድል ሊባል የሚችል መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም እነሆ በመነሻው ወቅት ለብዙዎች ህልም ይመስል የነበረው ትልማችን ዛሬ ወደሚታይና ወደሚዳሰስ ተጨባጭ ልማት ተቀይሮ በአሁኑ ጊዜ የግድቡ ግንባታ 56 በመቶ ሊደርስ መቻሉን አንስቷል ፡፡
ከጅምሩ አንስቶ የታየው ህዝባዊ ተሳትፎና ድጋፍ አሁንም ቢሆን በከፍተኛ ግለት የቀጠለ መሆኑን ነው የጠቀሰው ፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት መላው ህዝባችን በቦንድ ግዢና ልገሳ እንዲሁም ሌሎች ድጋፎች ባደረገው ርብርብ ከ9ነጥብ6 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ማሰባሰብ መቻሉንም እንዲሁ፡፡
ግድቡ በደለል እንዳይሞላም የአገራችን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከቦንድ ግዢ በተጨማሪ በዓመት ከ30 የስራ ቀናት በላይ በእርከን ስራ ላይ በመሰማራት በቢሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን አስረድቷል፡፡
ባለሃብቶች፣በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እያደረጉ በግድቡ ላይ የበኩላቸውን አሻራ በማኖር ላይ ናቸው ነው ያለውቅ ፡፡
የኢፌዴሪ መንግሥት በበኩሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ከማስተባበርና የግንባታውን ሂደት ከመምራት ባሻገር፡ ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር በሳል የዲፕሎማሲ ግንኙነት ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውቋል ።
በዚህ ጥረትም የታችኛው የተፋሰሱ አገራት፡ ግድቡ በውሃ አጠቃቀማቸው ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስባቸው እየተገነዘቡ መምጣታቸውን ገልጿል ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በአንድነት ያሰለፈ፤ ለዘመናት ተጠናውቶን የነበረውን ‹የአልችልም› መንፈስ የሰበረና በምትኩ የይቻላል መንፈስን ያቀዳጀ የዘመናችን ታላቅ ገድል መሆኑን አስገንዝቧል ።
አገራችንን ወዳሰብንበት የእድገት ከፍታ ለማውጣት መንግሥትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘው እየፈጸሙት ያለውን አስደማሚ ገድል አጠናክረን እንድንቀጥል የኢፌዴሪ መንግሥት ጥሪውን አስተላልፏል ።
የኢፌዴሪ መንግስት ለመላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እንኳን ለበዓሉ አደረሳችሁ እያለ በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን አቅርቧል ።