ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዛምቢያ የነበራቸውን የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አጠናቀው ታንዛኒያ ገብተዋል ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛምቢያ ጉብኝታቸውን ሲያጠናቅቁ እንደ አቀባበሉ ሁሉ በፕሬዝዳንት ኤድጋር ቻግዋ ሉንጉ የተመራ ደማቅ አሸኛነት የተደረገላቸው ሲሆን ስለተደረገላቸው መልካም አቀባበልና ቆይታም የአገሪቱን ህዝብና መንግስት አመስግነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሉሳካ ቆይታቸውን አጠናቀው ለተመሳሳይ የስራ ጉብኝት ዛሬ ወደ ታንዛኒያ ዳሬሰላም አምርተዋል።
ጁሊየስ ኔሬሬ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆን ፖምቤ ጆሴፍ ማጉፉሊ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን ለክብራቸውም 19 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል።
ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር በተለያዩ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይም መክረዋል።
ሁለቱ አገራት በቱሪዝም፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን በመከላከል፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ዘርፎች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል።
እንደ ጎርጎሮሲያን አቆጣጠር በ1961 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነጻነቷን የተጎናጸፈችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛኒያ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ መስኮች በጋራ እየሰራች ነው(ኢዜአ )።