ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በስድስት ዓመታት የግንባታ ሂደት በጥራትና በጥሩ ዲሲፕሊን በመካሄዱ ወደ ስኬት ማማ ለመድረስ የሚያስችል በመሆኑ ቃላችንን ጠብቀን ጠንክረን እንቀጥል ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።
አቶ ደመቀ የግድቡን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለአዲስ ዘመን እንዳመለከቱት፤ ግንባታው በተካሄደባቸው ዓመታት ውስጥ የሕዝቡ ተነሳሽነትና ባለቤትነት ስሜት ግለቱን እንደጠበቀ ቀጥሏል፡፡
በዚህ ጉዞ ውስጥ ውስብስብ የሆነውን ፕሮጀክት በጥራትና በጥሩ ዲሲፕሊን እዚህ ደረጃ ላይ ማድረስ መቻሉ የስኬትና ኩራት ምንጭ ነው ብለዋል ።
በግንባታው ሂደት የታየው ዋናው ጥንካሬ የህዝቡ የባለቤትነት መንፈስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሥራውን ለመምራት የፕሮጀክት ማኔጅመንቱ፣ የሀብት አሰባሰቡ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሥራው የሚጠይቀውን ሁሉ በቁርጠኝነት ለመፈፀም እየተደረገ ያለው ርብርብ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል ።
የግንባታው ሂደት ስኬታማነትና ውጤታማነት ምንጭ የመንግሥትና የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጁ ሳይሆን የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጥረት መሆኑን ጠቅሰው፤ «በዓሉ በድል እና በስኬት ላይ ሆነን የደረስንበት ነው። ስድስቱም ዓመት ሥራው ግለቱን ጠብቋል። የጀመርነውን ለመጨረስ ወደከፍታው ተቆናጠናል፤ ዳር ለመድረስ ግለታችንን ጠብቀን ልንቀጥል ይገባል፣ ሁሉም በዚህ ዙሪያ የድርሻውን ይወጣ፤ ቃላችንን እንጠብቅ» ሲሉም አሳስበዋል።
በተለይም የሠራተኛው የቦንድ ግዥ እጅግ ውጤታማ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከግል ባለሀብቱ ቃል የተገባው ግን ሙሉ ለሙሉ ገቢ አለመሆኑን አስታውሰዋል።
«ይሁንና ከ10 ሚሊዮን ብር ጀምረው እስከ ግማሽ ቢሊዮን ብር ድረስ ቃላቸውን የጠበቁ ባለሀብቶች እንዳሉም ሊሰመርበት ይገባል» ብለዋል። በቃላቸው ያልተገኙት ቃላቸውን ይተገብሩ ዘንድ የሚያስችል የማስታወስ ሥራ እንደሚሠራም አመልክተዋል።
በዳያስፖራው በኩልም የአንዳንድ አገራት ህግ የቦንድ ግዥ ለማካሄድ የማያስችል መሆኑን አስታውሰው፤ ነገር ግን ሁሉም በሮች ባለመዘጋታቸው በወኪሎቻቸው፣ አገር ቤት ሲመጡና በተለያዩ መንገዶች በህዳሴው ግድብ ላይ አሻራቸውን ሊያስቀምጡ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ አስታውቀዋል።
የግድቡን ዳር መድረስ የማይፈልጉ ኃይሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ በህዝቡ አንድነትና ጥንካሬ፣ መንግሥትም ያሉበትን ችግሮች ፈትቶ ጠንክሮ በመቆም የሚመከቱ መሆናቸው አስረድተዋል።
«በቀጣናው ውስጥ ጠንካራ ሀገር ሆነን እንዳንወጣ የሚደረግ የክፋትና የአጥፊነት ጥንስስ ሁልጊዜ ነቅቶ መጠበቅና መቋቋም ይገባል» ብለዋል፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የግብፅ ህዝብ እንዲህ ዓይነት ምክንያታዊ ጉዳይ አይቃወምም።
ዋናው የአስተምህሮና የተግባቦት ጉዳይ ነው። እስኪ አብረን እንደግ፣ ኢትዮጵያዊያን ተደጋጋሚ በሆነ መልኩ በድርቅ እየተጎዱ ነው።
በከፋ ድህነት ውስጥ ስላሉ ይህን የተፈጥሮ ሀብትን አልምቶ መጠቀም ሌላውን እስካልጎዳ ድረስ ምንድነው ጉዳቱ? ቢባል በየትኛውም መመዘኛ ሊገፋ የሚችል እውነት አይደለም ነው ያሉት ።
ስለዚህ በዚህ ደረጃ ህዝብን ለይቶ ከመንግሥት ጋር ያለውን እና የጥቂት ቡድኖች ጉዳይ በየራሳቸው ባህርይ በመያዝ በጥበብ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ያስፈልጋል ሲሉ ያስገነዘቡት-(አዲስ ዘመን) ፡፡