የትምክተኝነት አመለካከትን በብቃት ለመታገል የሚያስችል ቁመና ላይ መድረሱን ብአዴን አስታወቀ

በጥልቅ ታሃድሶው የኪራይ ሰብሳቢነትን ፣ የትምክተኝነት አመለካከትንና አስተሳሰብን በጠራ መንገድ ለመታገል የሚያስችል ቁመና ላይ መድረሱን የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ባለፉት ስድስት ወራት መደበኛና በጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው የደረሰባቸውን የግምገማ ውጤት ለአመራሩ ይፋ የተደረገበት መድረክ ትናንት በደብረማርቆስ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ የብአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ  አቶ አለምነው መኮነን እንደገለጹት፤ ከፍተኛ አመራሩ መላ ህዝቡን በማሳተፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ደረጃ በደረጃ የመፍታት አቅጣጫ መከተል አለበት።

የመድረኩ አላማም ባለፉት ስድስት ወራት በመደበኛና በታሃድሶ ንቅናቄው የተደረሰባቸውን ድምዳሜዎችና ውጤቶች ለአመራሩ በማሳወቅ እስከ ታች ድረስ ለማውረድ መሆኑን ገልጸዋል።

በጥልቅ ታሃድሶው የኪራይ ሰብሳቢነትን ፣ የትምክተኝነት አመለካከትንና አስተሳሰብን በጠራ መንገድ ለመታገል የሚያስችል ቁመና ላይ መድረሱን ማዕከላዊ ኮሚቴው መገምገሙ ጠቅሰዋል፡፡

"ይህም የድርጅቱን መርሆዎች በመጨበጥ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን  ለመመለስ  አንድ ምዕራፍ የተሻገርንበት ነው" ብለዋል።

የመካከለኛ አመራሩ በቀጣይ የመሰረታዊ ድርጅትና የህዋስ አደረጃጀቶችን ዋና የመተጋገያ መድረክ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል፡፡

ይህም ችግር ያለባቸውን አመራሮችን በየጊዜው ለማረም፣ በጥፋታቸው በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ፣ አድርባይነትን ለማስወገድ፣ የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራን ለማቀላጠፍ የተቀመጠው ነው ተብሏል፡፡

የህዝቡን የመልካም አስተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ትግሉ ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞን የብአዴን ጽፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ፤ " በቀጣይ ህዝብን በቅንነት በማገልገል፣ ችግሮችን ፈጥኖ በማረምና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ በጥራት በማከናወን የመልካም አስተዳደርን ለማስፈን ቁርጠኛ አቋም እንድይዝ አግዞኛል "ብለዋል።

በደብረ ማርቆስ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው  መድረክ ከ200 በላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስረዳደር አመራሮች ተገኝተዋል -(ኢዜአ)፡፡