የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ይገባሉ።
ፕሬዚዳንቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተደረገላቸው ግብዣ ነው ዛሬ ለጉብኝት አዲስ አበባ የሚገቡት።
ሁለቱ አገሮች የረጅም ዓመታት ታሪካዊና ባህላዊ ግንኙነት አላቸው።
የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት፤ ሁለቱ አገሮች ከህዝብ ለህዝብ ወዳጅነታቸው ባለፈ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል።
አገሮቹ የንግድ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር በመንገድ መሰረተ ልማት የጀመሩትን ትስስር በባቡር መስክም ለመድገም መታቀዱን ዶክተር ነገሪ ገልጸዋል።
ኢትዮ – ሱዳን ያላቸው ግንኙነት ለሌሎች አገሮች ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በምታካሂደው የልማት እንቅስቃሴ የሱዳን ድጋፍ እንዳልተለያት ነው የገለጹት።
አገሮቹ የዓባይ ወንዝን በፍትሃዊነት መጠቀም ላይ የጋራ መግባባት እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።
በፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ሁለንተናዊ ግንኙነት የሚያጠናክሩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ይፈረማሉ ተብሎ ይጠበቃል(ኢዜአ)።