የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በብሔራዊ ቤተ-መንግስት ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምምነቶች እንደሚፈራረሙም የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ሁለቱ አገራት ለረጅም ጊዜ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የነበረውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከርና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ያለመ መሆኑን ነው ያብራሩት።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር በማህበራዊ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በመሰረተ ልማት ያላትን ግንኙነት በማጎልበት የሁለቱን ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ለማጠናከርም ውይይት ይደርጋል ብለዋል።
የአባይ ወንዝን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ድጋፍ ከሚሰጡ አገራት መካከል ሱዳን አንዷ መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም አንዱ የውይይቱ አካል እንደሚሆን ተናግረዋል-(ኢዜአ) ።