የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘመኑ ከደረሰበት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ ጋር እኩል እንዲራመዱ የጀመራቸውን የድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
የምክር ቤቱ የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙኃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጽህፈት ቤቱን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አድርጓል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ እንደገለጹት፤ በህዝብ፣ በመንግስትና በግል መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ የመረጃ ፍሰት እንዲኖርም እየሰራ መሆኑንና የጀመረው ሥራና የሚሰጠውን የድጋፍና አቅም ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ።
ጽህፈት ቤቱ ዘመኑ ከደረሰበት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪ ጋር እኩል የሚራመድ ተቋምና ሚዲያ ለመፍጠር የአሰራር፣ የሰው ኃይል ማብቃትና የአደራጃጀት ማሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት ።
በአገር ውስጥ የሚገኙ የውጭ አገር የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመርኩዘው እንዲዘግቡና የአገሪቱን ገጽታ እንዲገነቡ ድጋፍና ክትትል መደረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ጽህፈት ቤቱ የአገሪቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራ በጥናትና ምርምር የተደገፈ እንዲሆን የሚዲያ ጥናትና ምርምር ተቋም እንዲቋቋም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የተቋማት ኃላፊዎች ለህዝብ ግንኙነት ሥራና ባለሙያዎች ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን የሰው ኃይልና ቁሳቁስ እንዲያሟሉ ምክክርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲሰሩም አመልክተዋል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ተቋማት መንግስትና ህዝብ የሚፈልገውን መረጃ በወቅቱ፣ በጥራትና በፍጥነት እንዲለቁ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አቅም የማጠናከርና አቅጣጫ የመስጠት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ጽህፈት ቤቱ ከፌደራል እስከ ክልል ቀበሌ ድረስ ባሉት መዋቅሮች ደረጃውን የጠበቀና ለጥቃት ያልተጋለጠ መረጃ ወቅቱን ጠብቆ ለማድረስ እየሰራ ቢሆንም በሚያጋጥሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች በስፋት መስራት አልተቻለም ብለዋል።
በየተቋማቱ የተሟላ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ ቁሳቁስና ቢሮ ያለመኖር እንዲሁም በረቂቅ ደረጃ የተዘጋጁት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ፖሊሲዎችና ደንቦች በወቅቱ ጸድቀው ወደ ተግባር ያለመግባት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የሰራተኛ ፍልሰት፣ የመስክና የከተማ ተሽከርካሪዎች እጥረት፣ የዘመናዊ መሳሪያዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖር ችግሮች በመፍታት የበለጠ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል ።
በተለይም የገጽታ ግንባታ ሥራን በስፋት ለማዳረስ ትክክለኛ መረጃ ለውጭ ጋዜጠኞች ለመስጠትና በውጭ የሚገኙ ኤምባሴዎችን ለመጠቀም የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሰሩም አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት፣ የኢኮኖሚ እድገቱና የዜጎች ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ ሕዝቡ ቅሬታ የሚያነሳባቸውን ዘርፎች በዳሰሳ ጥናት ለይቶ አስፈላጊውን መለስ ማሰጠት በቀጣይ ከሚሰሩ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አመልክተዋል- (ኢዜአ) ።