የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መከታተልና መመርመር የሚያስችሉ አዳዲስ የክትትልና የምርመራ መመሪያዎች አዘጋጀ።
ኮሚሽኑ ባዘጋጃቸው ሁለት አዳዲስ መመሪያዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አካሂዷል።
ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሔር እንደገለፁት መመሪያዎቹ በአገሪቱ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ላይ ጠንካራ ክትትል እና ምርመራ ለማድረግ ያስችላሉ።
በተለይም የምርመራ መመሪያው ኮሚሽኑ የሚቀርቡለትና በራሱ ተነሳሽነት የሚመረምራቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በብቃትና በጥልቀት ለማከናወንና በመላው አገሪቱ ተደራሽነቱን ለማሳደግ እንደሚያግዘው ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
በፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች እንዲሁም በፍርድ ቤት ከሚታዩ የሕግ ጉዳዮች ውጪ ማንኛውንም የመብት ጥሰት ኮሚሽኑ እንደሚመረምር አገራዊና ዓለም አቀፍ ህጎችን መሰረት አድርጎ የተዘጋጀው መመሪያ አስፍሯል።
በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ በሚያከናውናቸው ምርመራዎች ምክር ሐሳብ የመጠየቅና የማቅረብ እንዲሁም ክስ የመመስረት ሥራዎችን መፈጸም ያስችለዋል።
በሴቶች፣ በህፃናት፣ በአካል ጉዳተኞች እንዲሁም ለሰብአዊ መብት ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ ዜጎች ላይ የሚከሰቱ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንዲመረመሩ ዕድል የሚሰጥ ነው።
በምክክሩ የተገኙ ተሳታፊዎች ሁለቱ መመሪያዎች ኮሚሽኑ የሚያከናውነው የክትትልና የምርመራ ስራ ይበልጥ ጠንካራና ተአማኒ እንዲሆን የሚያስችሉ መሆናቸውን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።
በምክክሩ በተገኙት ግብአቶች መመሪያዎቹን እናጠናክራለን ያሉት ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ዳብረው በቀጣይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንደሚያጸድቁ አስታውቀዋል(ኢዜአ) ።