ኳታር በግብርና ዘርፍ እንድትሰማራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቀረቡ

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የኳታር ባለኃብቶች በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ  የኳታር አሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ትሃኒን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በምጣኔ ኃብታዊ ዘርፍ በተለይም በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች በኳታር የገበያ እድል አንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በማዕድንና በአገልግሎት ዘርፍ በሥፋት በመሰማራት የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የኳታር አሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ትሃኒን በብሄራዊ ቤተመንግስት ተቀብለው ያነጋሩት ፕረዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው  የኳታር ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ የአገሪቷን ልማት እንዲደግፉ ነው የጠየቁት ።

ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ አገሪቷ የምታደርገውን የዕድገት እንቅስቃሴ በመደገፍ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል ።

በፖለቲካው ረገድም ይበልጥ በመሥራት ግንኙነቱ አሁን ካለበት ደረጃ ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል ።

በዚህም ኢትዮጵያና ኳታር በትብብር መስራት የሚያስችሏቸውን በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶች መፈራረም መቻላቸው ተመልክቷል ።

በሁለቱ አገራት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የተደረሱ ሥምምነቶችን ገቢራዊ በማድረግ ምጣኔ ሃብታዊ ውህደቱን ማፋጠን እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል ። 

የኳታር አሚር ሼህ ታሚም ቢን ሃማድ አል-ትሃኒ በበኩላቸው የአገራቱን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር የሚቻላቸውን ሁሉ እንደሚሰሩ ነው ያረጋግጡት ፡፡

በምጣኔ ሃብታዊ ዘርፍ፤ በተለይም በኢትዮጵያ የሚመረቱ የግብርና ውጤቶች በኳታር የገበያ እድል አንዲያገኙ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል ፡፡

ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ደህንነት እንዲረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ነው የገለጹት።

በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመመከት የሠብዓዊ ዕርዳታ ቡድን በመላክ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ዕቅድ እንዳላቸውም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ኳታር ከዚህ ቀደም በአገራቱ ባለሙያዎች መካከል የሚደረጉ ድርድሮች አሁን ላይ በሚኒስትሮች አሊያም ደግም በመሪዎች ደረጃ እንዲደረግ ተስማተዋል።

ሁለቱ አገራት ከዚህ በፊት የነበራቸው ግንኙነት የተቋረጠው የኳታር መገናኛ ብዙኃን አል-ጄዚራ አሸባሪ ተብለው የተሰየሙ ድርጅቶችን እንደሚደግፉ በመግለጻቸው ነበር ።

ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ ድርጊቱን በመቃወም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2008 እንዲቋረጥ ማድረጓም ይታወሳል ።

የኢትዮጵያና ኳታር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1995 እንደነበር የሚታወቅ ነው ።