በ8ኛው ዙር የፓርቲዎች ውይይት የድርድርና አሠራር ደንብ ፀደቀ

በትናንትናው ዕለት በተካሄደው 8ኛው ዙር አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት   የፓርቲዎች የድርድርና አሠራር ደንብ ፀደቀ  ።

 በፓርቲዎቹ ውይይት ወቅት የአደራዳሪ፣የታዛቢ ፣ ስነ ምግባር፣ የሚዲያ ፣ የውስጣዊ አደረጃጃትና የግብዓት አቅርቦትና የመደራደሪያ ቦታን በተመለከቱ ጉዳዮች  ላይ የተለያዩ  ሓሳቦች በፓርቲዎቹ ተሠንዝረዋል ።

በተለይ  አደራዳሪ ማን ይሁን ፣ የሚዲያ ሽፋንና የመደራደሪያ ቦታው የት ይሁን  የሚሉት  ነጥቦች ትኩረት ተሠጥቷቸው ጥልቅ ክርክር የተደረጉባቸው ጉዳዮች ናቸው ።

የፓርቲዎቹ አደራዳሪ ከሦስተኛ አካል ውጭ ከራሳቸው ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላትን በመመርጥ ለመደራደር ተስማምተዋል ።  

ሆኖም  ማን እንዴት ያደራድር በሚለው ሐሳብ ከፓርቲዎቹ  መካከል መኢዴፓ ያልተስማማ በመሆኑ ምክንያት ሐሳቡ  በልዩነት  እንዲመዘገብለት ተደርጓል ።

የፖለቲካ  ፓርቲዎች ለድርድር ከመግባታቸው በፊትና ከድርድሩ ከወጡ በኋላ ለሚዲያ የሚሠጠው መረጃ  በሚመለከተው አካል ብቻ መሠጠት እንዳላበት በውይይቱ ተስማምተዋል ።

የፓርቲዎቹ ድርድሩ  የት ይሁን በሚለው ነጥብ ላይ ኢዴፓና መኢአድ ለነጻነትና ለገጽታ ግንባታ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ አዳራሽ ወይም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ መሆን አለበት የሚል አቋም አንፀባርቀዋል ።

ቅንጅት ፣ አንድነት ፣ አትፓ፣ ኢራፓ እና ኢህአዴግ ከሉዓላዊነት አንፃር የተለያዩ ሓሳቦችን በማንሳታቸው ድርድሩ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ይካሄድ የሚለው ሚዛን በመድፋቱ በምክር ቤት እንዲካሄድ  ስምምነት ላይ ተደርሷል ።