የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በአዲስ አበባ ለሚገነባው የዋና መስሪያ ቤት ህንጻ የመሰረት ድንጋይ ተጣለ።
በስነ-ስርዓቱ ላይ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ዛሬ የተገኙ ሲሆን የሚገነባው ህንጻ ''የኦሮሚያ ሚዲያ ኮምፕሌክስ'' የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
በ4 ሺህ 482 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ባለ 14 ፎቅ የሚዲያ ኮምፕሌክስ ግንባታ በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ የክልሉን ሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም መሠረት አድርጎ የሚሰራና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ መገናኛ ብዙሃን የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ባለፉት 10 ዓመታት ክልሉን በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ እንደ ሚዲያ አንግቦ ከሚንቀሳቀሰው ዓላማ አንጻር ብዙ ስራዎች የሚቀሩት በመሆኑ ተግባሩን በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠን የሰው ኃይል ማስኬድ ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ "የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የኦሮሚያ ሚዲያ ኮምፕሌክስ መገናኛ ብዙሃኑን ለማዘመን ወሳኝ ሚና ይጫወታል" ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ወዬሳ በበኩላቸው ዋና መስሪያ ቤቱን ወደ አዲስ አበባ ማምጣት ያስፈለገው ከተማዋ የክልሉ መንግስት ዋና መስሪያ ቤቶች፣ የፌዴራልና የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮምፕሌክሱ ግንባታ በሁለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ዲዛይኑ በሶፍ ኡመር ዋሻ ተምሳሌት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
"የሚዲያ ኮምፕሌክሱ ግንባታ ሁሉንም ዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች መጠቀም የሚያስችል ነው" ያሉት ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብይ አህመድ ናቸው ።
በተለይም አዲሱን ሚዲያ በአግባቡ ለመጠቀም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የሚዲያ ኮምፕሌክስ ነው ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና መስሪያ ቤቱን አዳማ ላይ በማድረግ ላለፉት አስር ዓመታት በቴሌቪዥንና በሬዲዮ መረጃዎችን በማሰራጨት ላይ ይገኛል-(ኢዜአ) ።