በመላ አገሪቱ በኢህአዴግ መሪነት ለወራቶች ሲካሄድ የቆየው ጥልቅ ተሃድሶው ሂደት ጥራቱን በጠበቀ ሁኔታ መከናወኑን የኢህአዴግ ምክር ቤት አስታወቀ ።
የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ለዋሚኮ እንደገለጹት የኢህአዴግ ምክር ቤት ባለፉት 15 ዓመታት በአገር ደረጃ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ፈተናዎችን በጥልቅ ገምግሟል ።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በዘንድሮ ዓመት በአገሪቱ በየደረጃው የተከናወነው የመታደስ ሂደት በጥራት መካሄድ መቻሉን አረጋግጧል ብለዋል አቶ ሽፈራው ።
ባለፉት ወራት የተካሄደው ጥልቅ ተሃድሶው በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን ስጋት መቀልበስ ያስቻለ መሆኑን አቶ ሽፈራው ጠቁመዋል ።
የኢህአዴግ ምክር ቤት በጥልቅ ግምገማውም ሆነ በሰሞኑ ግምገማ ባስቀመጠው አቅጣጫ የመልካም አስተዳደር፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነትና የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ በቀጣይ ትኩረት የሚሠጥባቸው ጉዳዮች መሆኑን ማስታወቁን አቶ ሽፈራው አመልክተዋል ።
ምክር ቤቱ የመልካም አስተዳደር ችግርን ፣ ያልተገባ ጥቅም ፈላጊነት አባዜንና የወጣቶች የሥራ ማጣት ችግር ለመፍታት በፍጥነት ተጨባጭ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባት እንደሚያስፈልግ አጽዕኖት መሥጠቱን ዋልታ ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ኮርፖሬት ዘግቧል ።