ሃይማኖታዊ መረዳዳትን ማጠናከርና ማጎልበት ይገባል

በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ  አቋም መግለጫ  ከብዝሃነት መገለጫዎቻችን አንዱ ከሆነው ሃይማኖት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የእርስ በእርስ የመረዳዳት ባህላችንም አብዝተን ልንኮራበት የሚገባን የኢትዮጵያውያን ልዩ መገለጫ እሴታችን  መሆኑንና ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክቷል።

የሰው ዘር መገኛ፣ የበርካታ ሃይማኖቶችና እምነቶች እንዲሁም የልዩ ልዩ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ ለዓለም በርካታ እሴቶችን አበርክታለች።

ከእነዚህ እሴቶች መካከልም የሃይማኖት መቻቻል ተጠቃሽ መሆኑን መግለጫዉ ያትታል።

እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚከበሩ በርካታ ሃይማኖታዊ በዓላት አሏት። እነዚህ በዓላት ከሃይማኖታዊ ፋይዳቸው ባሻገር የህብረተሰባችን የመረዳዳት ባህል እና የአብሮነታችን መገለጫዎች ሆነው የሚያገለግሉን በመሆናቸው ሁሌም ልንንከባከባቸውና ልንጠብቃቸው የሚገቡ ብርቅየ እሴቶቻችን ናቸው።
ከዚህ አንጻር ዛሬ የተከበረው የስቅለት በዓል እና ከነገ ወዲያ እሁድ የሚከበረው የትንሳኤ በዓል በህዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሃይማኖታዊ በዓል እንደመሆኑ የኢፌዴሪ መንግሥት በዚህ አጋጣሚ ለመላው ህዝበ ክርስቲያን እንኳን በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልጻል።

በዓሉ በተረጋጋ ሁኔታ በድምቀት ይከበር ዘንድ መንግሥት አስፈላጊውን ዝግጅት ያደረገ ሲሆን ህዝበ ክርስቲያኑም ለበዓሉ ስኬትና ድምቀት ከጸጥታ ሃይሎች ጎን በመቆም የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪውን እያቀረበ ከማንነታችን መገለጫዎች አንዱ የሆነው የትንሳኤ በዓል የተሳካና የደመቀ እንዲሆንላችሁ በድጋሚ ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል።