የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋህአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጉባኤ አቶ ጋትሉዋክ ቱት የድርጅቱን ዋና ሊቀመንበር አድርጎ መረጠ።
የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራሮቹን የመረጠው ከትናንት በስትያ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በጥልቅ ተሃድሶ ግምገማው የተሻለ ዓቅምና የጠራ አመለካከት ያላችውን ቀደም ሲል የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ጋትሉዋክ ቱትን ዋና ሊቀመንበር አቶ ሰናይ አኮዎርን ደግሞ ምክትል አድርጎ በመመረጥ ሰይሟል።
የድርጅቱ አዲሱ አደረጃጀት የብሄረሰብ ስብጥርን ሳይሆን ብቃትን መሰረት ያደረገ እንደሆነም በመድረኩ ላይ ተግልጿል።
የድርጅቱ ሊቀመንባር ሆነው የተመረጡት አቶ ጋትሉዋክ ቱት እንደገለጹት፤ ድርጀቱ የጀመረውን ልማታዊና ዴሞክራሲዊ መስመሮች አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራሉ።
የህዝቦችን አንድነት ይበልጥ በማጠናከር በተለይም በወጣቱና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
እንዲሁም በመንደር የተሰባሰበው ህዝብ ይበልጥ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩት ስራዎች ተጠናክርው እንደሚቀጥሉም አቶ ጋተሉዋክ አረጋግጠዋል።
የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንባር አቶ ሰናይ አኮዎር በኩላቸው የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማጎልበት ድርጅቱ የጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩን ኦቡያ በበኩላቸው " ቀጣይነት ያለው የተሀድሶ ግምገማ በማካሄድ ድርጅቱን አቅም ባላቸውና የጠራ የአመለካከት መስመር በያዙ አመራሮች የመገንባቱ ሂደት ተጠናክሮ ይቀጥላል "ብለዋል።
የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጋህአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ በየሶስት የብሄረሰብ ዞኖች የተካሄደውን ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ሪፖርት በመገምገም ነው ጉባኤውን ያጠናቀቀው- (ኢዜአ) ።