የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም …ጥናት 

 

የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት አለማምጣቱን የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አስታወቀ ።

ማዕከሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "በትምህርት ተቋማት የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ግንባታና ዴሞክራሲያዊነት፣ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች" በሚል ርዕስ የተካሄደ ጥናት ትናንት ውይይት ተደርጎበታል።

የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ባካሄደው ጥናት "ከአምስተኛ ክፍል ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በአመራር ድክመት የሚጠበቅውን ውጤት አላስገኘም"።

የትምህርት ዘርፉ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር መምራት አለመቻሉን ነው ጥናቱ ያመለከተው።

የመማሪያ መፅሐፉ ይዘት የተደጋገመ መሆን፣ አቀራረቡ ከዓላማው ጋር መቃረኑ እና የትምህርቱ መርሀ ግብር የሚመራበት በቂ አደረጃጀትና አሰራር አለመኖሩ በቁልፍ ችግርነት በጥናቱ ተጠቅሷል።

ትምህርቱን ለሚሰጡ መምህራን ከፍተኛ ትኩረት መስጠትና ማብቃት እንደሚያስፈልግም ነው የተመለከተው።

በመድረኩ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደገለጹት፤ በስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ላይ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ የተቀናጀ ስራ ባለመሰራቱ የሚፈለገው ውጤት ያለመምጣቱን ነው ያረጋገጡት ።

በጥናቱ የቀረበው ችግር በስነ ዜጋና ስነ ምግባር የታየ ችግር ብቻ ሳይሆን በትምህርት ጥራት ላይም ችግር እየፈጠረ መሆኑን ነው የገለጹት።

በጥናቱ የቀረቡ ችግሮችን በመያዝ "መፍትሔ የመስጠት ሥራ መሰራት አለበት" ነው ያሉት።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኣባይ ጸሃየ በበኩላቸው ፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት ያለማምጣት ቁልፍ ችግር የአመራሩ ድክመት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት ።

አቶ በረከት ስምዖንም  ችግሩ የአመራር ውድቀት መሆኑን ገልፀው፤ "የማስተካከል ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል" ብለዋል።

"መምህሩ ለለውጥ የተዘጋጀ ኃይል ነው" ያሉት አቶ በረከት፤ እሰካሁን ለውጥ ያልመጣው የአመራር ሁኔታው ችግር ስላለበት መሆኑን አመልክተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም በሰጡት አስተያየት፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ ያስፈልጋል።

የመገናኛ ብዙሃን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፎ ደካማ መሆኑ በጥናቱ ውስጥ መገለፁን ያደነቁት ዶክተር ሂሩት፤ "አሁን ያላቸውን ሚና ለማሳደግ መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው፤ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ስርዓተ ትምህርትን በማሻሻል "በሚቀጥለው ዓመት ወደ ተግባር" እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ጥናቱ የሸፈናቸው አካባቢዎች የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ብሄር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ሶማሌ ክልሎች እና አዲስ አበባ አስተዳደር ናቸው።

የጥናትና ምርምር ማዕከሉ ላለፉት ሦስት ዓመታት ባካሄደው እንቅስቃሴ በተለያዩ ዘርፎች ወደ 14 የሚጠጉ ጥናቶችን አካሂዷል።

ጥናቱ የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት ስርዓተ ትምህርት እንዲከለስ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል- (ኢዜአ ።