የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአገሪቷ ተከስቶ በነበረው አለመረጋጋት ዙሪያ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲቀርብ ለህግ፣ፍትህና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመራ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽኑ ባቀረበው ሪፖርት ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ነው የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርብ ለቋሚ ኮሚቴው የመራው።
በዚሁ መሰረት ለቋሚ ኮሚቴው ውሳኔ ቁጥር 11/2009 ሆኖ ተመርቷል።
ኮሚሽኑ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች ከሰኔ 2008 ዓ.ም እስከ መስከረም 2009 ዓ.ም የተከሰተውን ሁከትና ብጥብጥ አስመልክቶ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ምክር ቤቱ ተወያይቶበታል።
አባላቱም በሪፖርቱ ላይ መካተት በሚገባቸውና ግልጽነት በሚጠይቁ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተዋል።
“ለምን የኮንሶ ጉዳይ በሪፖርቱ አልተካተተም?፣ የተወሰደው እርምጃ ምን ያህል ሚዛናዊ ነው? ፣ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ዙሪያና በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን የደረሰው የንብረት ውድመት ለምን በባለሙያ አልተተመነም?” የሚሉ ከአባላቱ ከተሰነዘሩ ጥያቄዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ኮሚሽነሩ ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ የኮንሶ ጉዳይ በተገኘው የምርመራ ውጤት ላይ ኮሚሽኑ ከክልሉ መንግሥት ጋር ሁለት ጊዜ ውይይት አድርጓል።
በዚህም ''መንግሥት ምን ማድረግ እንዳለበት ምክረ ሀሳብ አቅርበናል'' ብለዋል።
በደቡብ ክልል ጌዲዮ ዞን በተፈጠረው አለመረጋጋት የወደመው ንብረት በዓይነት ሪፖርቱ ውስጥ መካተቱን ገልጸው፤ በትክክል የገንዘብ ተመኑን ለማወቅ በባለሙያ የተደገፈ ሥራ አለመሰራቱን ዶክተር አዲሱ ተናግረዋል።
''በኢሬቻ በዓል ላይ በመኪና ተጭነው ሲዘዋወሩ፣ መድረክ ላይ ወጥተው ሲቆጣጠሩ የነበሩ ኃይሎችን አስቀድሞ መቆጣጠር ይቻል ነበር'' ያሉት ኮሚሽነሩ፤ መንግሥት በመሰል ህዝባዊ በዓላት ላይ ችግሮች እንዳይከሰቱ የማድረግ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ላይ የነበረውን ሰብዓዊ መብት አያያዝ የሚያሳየውን የምርመራ ውጤት ማጠቃለያ ከየክልሎቹ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን አብራርተዋል።
እንደ ዶክተር አዲሱ ገለጻ፤ በተገኘው ውጤት ዙሪያ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢኖርም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ልዩነት ነበር።
''በኢትዮጵያ ሱማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ኮሚሽኑ ምርመራ አላካሄደም። ነገር ግን የኅብረተሰቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግ በአባባሽ ምክንያትነት በሪፖርቱ ውስጥ ተካቷል'' ብለዋል።
ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የመልካም አስተዳደር እጦትና መሰል ጉዳዮች ችግሩ እንዲፈጠርና እንዲባባስ ያደረጉ መሆናቸውን ነው ኮሚሽነሩ አጽንኦት የሰጡት-(ኢዜአ) ።