ሀገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የሚመሩበት የአሰራር ደንብ አጸደቁ

ኢህአዴግና ተፎካካሪ ሀገር ዓቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድር የሚመሩበት የአሰራር ደንብ በማጽደቅ አደራዳሪዎቻውንም መረጡ  ፡፡

በአዲስ አበባ ዛሬ ተወያይተው ያጸደቁት ደንብ ዋናውን የድርድር ሂደት ውጤታማ የሚያደርግ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሆደ ሰፊነት ድርድሩን ሁሉም ሊጠቀምበት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት ፡፡

እነዚህ ሃገር ዓቀፍ ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ኢህአዴግ የአሰራር ደንቡን ተከትለው ድርድሩን በቋሚነት የሚመሩ ሶስት ቋሚ አደራዳሪዎችን መርጠዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በተጨማሪም የድርድሩን አጀንዳ የሚያደራጁ ሶስት ሰዎችን የመረጡ ሲሆን፤ በስምንት ዙሪያ ደረጉትን የቅድመ ድርድር ቃለ ጉባኤም አጽድቀዋል ፡፡

በቋሚ አደራዳሪነት የተመረጡት ደግሞ አቶ አሰፋ ሀብተ ወልድ ከመኢአድ በሰብሳቢነት፤ አቶ ዋሲሁን ተስፋዩ ከኢዴፓ ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ፤ አቶ አለማየሁ ደነቀ ከአዲስ ትውልድ ፓርቲ በረዳት  ሰብሳቢነት በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው ፡፡

እነዚህ በአደራዳሪነት የተመረጡት ግለሰቦች በድርድሩ ሂደት የአደራዳሪነት ሚና ብቻ ሚጫወቱ ሲሆን፤ የፖለቲካ ፓርቲያቸውን በመወከል በተደራዳሪነት የማይቀርቡ መሆኑም ተገልጿል።

የፖለቲካ ፓርቲዎቹ የአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴም በዲሞክራሲያዊ አገባብ መርጠዋል።

የድርድሩ አጀንዳ አደራጆች አቶ አስመላሽ ገብረስላሴ ከኢህአዴግ፤ አቶ ገብሩ በርሄ እና አቶ መላኩ መሰለ ከተለያዩ ሃገር ዓቀፍ ተቀዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሆነው ተመርጠዋል፡፡

በምርጫው ወቅትም ፓርቲዎቹ እህአዴግ ድርድሩን የጠራ በመሆኑ በአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፍ ተስማምተዋል።

ፓርቲዎቹ በድርድር ደንቡ መሰረት ከነገ ጀምሮ በ15 ቀናት ውስጥ የመደራደሪያ አጀንዳዎቻቸውን የአጀንዳ አደራጅ እና የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ኮሚቴ እንደሚያስገቡም ታውቋል።

ዋልታ እንደዘገበው ከ15 ቀን በኋላም አደራዳሪ ኮሚቴዎቹ ቀን በመወሰንና ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ በማድረግ ስራቸውን እንደሚጀምሩም ነው የተመለከተው ።