መንግስት አሁንም ገና ባልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል -ጠቅላይ ሚኒስትር

መንግስት በጥልቅ ተሃድሶ የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመመለስ እንደሚሰራ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አስገነዘቡ ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ባደረጉት ቃለ ምልልስ  አሁንም የህዝብ ጥየቄዎችን ለመመለስ በጥልቀት መሄድ ይገባናል ብለዋል ፡፡

በተካሄዱት ጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች የተመለሱ አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይም ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች በልዩ ትኩረት ለመመለስ እንደሚሰሩ አስገንዝበዋል  ፡፡

ስለሆነም ያልተፈቱ ችግሮች ተስፋ ሊያስቆርጡ አይገባም ካሉ በኋላ መንንግስት ያጋጠሙ ችግሮች ህዝብንና ሲቪክ ማህበራት በማሳተፍ በሂደት እየተፈቱ እንደሚሄዱ ነው ያረጋገጡት ፡፡

እስከ አሁን በተደረጉ ጥረቶችም  ተሃድሶን በማጥለቅ ረገድ ትልቅ ድል መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል ፡፡

መንግስት በተለይም የወጣቶችን ጥያቄዎች ለመመለስ የተመደበው 10 ቢሊየን ብር ከሌሎች ጋር ማክሮ ፋይናሶች ጋር በመሆን በአነስተኛና ጥቃቅን በስፋት የሚገቡበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ ሌት ተቀን ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

የተወሰነ ቦታዎችን ተስፋ ሰጪ ተግባራት ይታያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር፤ በሌሎች አከባቢዎችም ከዚሁ ተሞክሮ መውሰድ ይገባቸዋል ነው ያሉት ፡፡

በሀገሪቱ መድብለ ፓርቲም ለማጠናከርም መንግስት ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጀመረው ድርድር  የመጓተት ሁኔታ ቢኖርም በታለመለት አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡

ከዲፕሎማሲ ስራዎች አንጻርም መቀመጫቸውን በግብጽ ካይሮ አድርገው በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ሁከት ሲመሩ በነበሩ ተቋማት ላይ የሀገሪቱ መንግስት አርምጃ መውሰድ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አስታውቀዋል ።

ሁለቱ ሀገራት በጋራ ባደረጉት ውይይት ነው ግብጽ በኢትዮጵያ አፍራሽ ሚናን የሚጫወቱ ተቋማትን ላለማስተናገድ ቃል መግባታቸውን ነው ያመለከቱት ።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት ለየት የሚያደርገው በትክክል መጠየቅ ያለባቸውን ሰዎች በግልፅ ማስቀመጡ ነው፤ ይህም የኮሚሽኑ አቅም እየጠነከረ መምጣቱን ያመለክታል ነው ያሉት ።

ግለሰቦቹን ተጠያቂ ከማድረግ አንጻርም መንግስት ምንም አይነት ችግር የለበትም፤ ሪፖርቱ ባስቀመጠው መልኩ መንግስት  አስፈላጊው ነገር ያደርጋል ሲሉም አስታውቀዋል ።

የኮሚሽኑ ገለልተኛነት በተመለከተም  “እኛ በዋናነት መታመን የምንፈልገው በህዝባችን ነው፤ በሁከቱ የደረሰው ጉዳት በአጠቃላይ በህዝቡ የሚታወቅ ነው ስለዚህ የሚደበቅም የሚሸፈንም ነገር የለንም” ሲሉ ነው ያስገነዘቡት ።

ሌሎች ተቋማት ጉዳዩን ለማጥናት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ መኒስትሩ ፤ ጉዳዩ እኛን የሚመለከት በመሆኑ እና የሉአላዊነት ጉዳይ በመሆኑ አልፈቀድንላቸውም ነው ያሉት ።

ኮሚሽኑ አጥንቶ ያቀረበው ሪፖርት በጄኔቫ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተቀብሎት እውቅና መስጠቱን እና ሁለቱ ተቋማት በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ከሶማሊያ ጋር ያለው ግንኙነትም ጠንካራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም ከአሚሶም ጋር በመሆንም ከዚያ ውጪም የሚሰራው ስራ ውጤታማ ስለሆነ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ፡፡