በድሬዳዋ አስተዳደር በ167 ሠራተኞችና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ ተወሰደ

 

በድሬዳዋ አስተዳደር ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት በሆኑ 167 የመንግስት ሠራተኞችና 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታወቀ ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሒም ዑስማን ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ አንድ ሶስተኛ በሚሆኑ የአስተዳደሩ አመራሮች ላይ እርምጃው የተወሰደው ባለፉት ሦስት ወራት ከከፍተኛ አመራር እስከ ሠራተኛው ድረስ በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ግምገማ ላይ የተለዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ ነው፡፡

በአስተዳደሩ 110 አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱንና ከነዚህም ውስጥ 13 አመራሮች ከስልጣናቸው እንዲነሱ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ሌሎች 22 አመራሮች ከከባድ እስከ ቀላል ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 31 የቢሮና የሴክተር መስሪያቤት አመራሮች እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል ብለዋል ።

በተጨማሪም 30 የቀበሌና 14 የገጠር ክላስተር አመራሮች በሚመጥናቸው ሥፍራ እንዲመደቡ መደረጉን ነው ያስታወቁት ።

በተጨማሪ ሕዝብን ለምሬትና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉ የነበሩና በሙስና ተግባራት የተሰማሩ 42 ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል ፡፡

75 ሠራተኞች ከቀላል እስከ ከባድ የዲሲፒሊን ቅጣት እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን 29ኙ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሸጋሸጉ ተደርጓል ነው ያሉት ።

በ21 ሠራተኞች ላይ መረጃ የማጥራት ሥራ እየተሰራ መሆኑንና በዘጠኙ ቀበሌዎች ደንብ በማስከበር ሥራ ላይ የተመደቡ ሁሉም በፈጠሩት ከፍተኛ ችግር ውላቸው ተቋርጦ እንዲሰናበቱ መደረጉን ገልጸዋል ።

በየደረጃው ከሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተካሄደው ጥልቅ የተሃድሶ ውይይት መድረክ ላይ አመራሩ በተሰጠው ሥልጣን ሕዝብን  ከማገልገል ይልቅ ራሱን ሲጠቅም መቆየቱን ነው ያስረዱት፡፡

በተጨማሪ ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር ህዝቡን ለከፋ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲዳርጉት መቆየታቸውን በግምገማው ተለይቷል፡፡

 ከድሬዳዋ ነዋሪዎች ውስጥ ወይዘሮ አሚና አሊ " እርምጃ መውሰድ መጀመሩ ጥሩ ነው፣ ነገር ግን ህዝቡን ለብሶት የዳረጉ አመራሮችና ሠራተኞች አሁንም አሉ፤ መንግስት እነዚህንም እየተከታተለ መስመር ማስያዝ አለበት" ብለዋል፡፡

አቶ አብዱሸኩር አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ያለበትን ችግር ለይቶ ከሕዝብ ለተነሱ የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት የወሰደው እርምጃ ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል-(ኢዜአ)፡፡