የብዙሃን ማህበራትን የዴሞክራሲ ስርዓት አቅም ለማሳደግ መንግስት በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንደሚያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አባ ዱላ ገመዳ ተናገሩ።
በሃገሪቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ የሲቪክ ማህበራት ተሞክሮ፣ ችግሮች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ይገኛል።
የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ እንዳሉት፥ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሲቪክ ማህበራት፣ የህዝብ አደረጃጀቶችና የሙያ ማህበራት ጉልህ ድርሻ አላቸው።
መንግስትም የዴሞክራሲ ስርዓቱ እንዲጎለብት በየደረጃው ላሉ ምክር ቤቶች እና ብዙሃን ማህበራት ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል።
ለዴሞክራሲ ስርዓቱ መጎልበትና መጠናከር የሚያደርገውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት አፈጉባኤው።
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ፥ የሲቪክ ማህበራትን አለም አቀፋዊ ባህሪ እና በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለውን ተሳትፎና አስተዋጽኦ በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቧል።
በጥናታዊ ጽሁፉ የሲቪክ ማህበራት ለዴሞክራሲያ ስርዓት ግንባታው አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ማህበራቱ የትኛውንም አይነት የፖለቲካ ርዕዮተ አለም በሚከተሉ ሃገራት ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ተነስቷል።
ዜጎች በተናጠል ፍላጎትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይልቅ በማህበራት በመሰባሰብ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ከፍ ያለ መሆኑም ነው በጥናታዊ ጽሁፉ የተነሳው።
በጥናታዊ ጽሁፉ በኢትዮጵያ የሲቪክ ማህበራት አስተዳደራዊ ወጪን ለማስተካከል የወጣው አዋጅ ክፍተት እንዳለበትም ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ማህበራቱ ከውጭ የሚያገኙት ድጎማ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአስተዳደራዊ ወጪያቸው ላይ ክፍተት ከመፍጠሩ ባለፈ፥ ማህበራቱ የአባላቶቻቸውን ጥቅም የማያስከበርላቸው በመሆኑ አዋጁ ሊሻሻል ይገባልም ነው የተባለው።
ይህም ከፅንፈኛ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ በመውጣት ግጭትን ለመከላከልና ጠንካራ የማህበረሰብ ትስስር ለመፍጠር ተብሏል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።