ኢትዮ- ሳት የተሰኘ ብሔራዊ የጋራና የተቀናጀ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፍ ተዘጋጀ።
የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በሳተላይት ቴሌቪዥን ሥርጭት ማዕቀፉ ላይ ዛሬ ከፌዴራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
ፕሮጀክቱ የሙከራ ሥርጭት ያደረገ ሲሆን፥ ከሚያዚያ 16 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ተግባራዊ ይሆናል ተብሏል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ እንዳስታወቁት ፤ማዕቀፉ የተዘጋጀው ሃገሪቷ በስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ካላት ፍላጎትና ከሚዲያ ኢንዱስትሪው መስፋፋት ጋር ተያይዞ ተነሳሽነቱን ለማስፋት ነው።
ኢትዮጵያ ጥራቱን የጠበቀ፣ በዋጋው ተመጣጣኝና ለምንም አይነት ጂኦፖለቲካል ተፅዕኖዎች ያልተጋለጠ የሳተላይት ማዕቀፍ እንዲኖራት ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
የጋራና የተቀናጀ የሳተላይት ቴሌቪዥን ስርጭት ማዕቀፉ የመገናኛ ብዙሃንን እኩልነት፣ ፍትሃዊነትና ተደራሽነት በማረጋገጥ በመረጃ የበለፀገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የጎላ ሚና ይኖረዋልም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ እስካሁን የራሷ ሳተላይት ስለሌላት በሃገሪቱ የነበሩ ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በየግላቸው የዓረብ፣ የናይልና ገልፍ ሳቶችና መሰል የውጭ ሳተላይቶችን ይከራዩ እንደነበር ተገልጿል።
ማዕቀፉ ተግባራዊ ሲሆን ሁሉም የቴሌቪዥን ቻናሎች በአንድ ማዕቀፍ የማሰራጨት ዕድል እንደሚኖራቸው ነው የተገለጸው።
የፕሮጀክቱ ኃላፊ ሻለቃ ገብረመስቀል ተክለማርያም በበኩላቸው፤ የማዕቀፉ መዘጋጀት ለሳተላይት የሚከፈለውን የውጭ ምንዛሪ ከመቀነስ ባሻገር ቻናሎቹ የሚያጋጥማቸውን የደህንነት፣ የተደራሽነት፣ የቴክኖሎጂ፣ ሞገድ አጠቃቀምና የጥራት ውስንነቶች የሚቀርፍ ነው ብለዋል።
በሃገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የህዝብና የመንግስት የቴሌቪዥን ቻናሎች በማዕቀፉ የሚካተቱ ሲሆን፥ በማዕቀፉ መጠቀም ለሚፈልጉ ለሃገር ውስጥ የግል የቴሌቪዥን ቻናሎች ግን በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ይሆናል ነው የተባለው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ የስርጭት ማዕቀፍ ተደራሽነቱ መካከለኛው ምስራቅ፣ ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራትና የተወሰኑ የአውሮፓ ሃገራትን የሚያካልል ነው-(ኤፍ ቢ ሲ) ።