ዲሞክራሲያዊ ተቋማት የህግ የበላይነት እንዲከበር የተጣለባቸውን ኃላፊት አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል -መንግስት

የዴሞክራሲ ተቋማት የህግ የበላይነት እንዲከበር የተጣለባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የፌደራል መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር አስገነዘበ ።

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዜጎች መብት መከበር የዴሞክራሲ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት አጠናክረው እንዲቀጥሉ  ነው ያሳሰበው ።

መንግሥት ራሱን በራሱ ማረም እንዲችል ነጻ ሆነው የተመሰረቱት የዴሞክራሲ ተቋማት  የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ ብሏል ።

ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለዜጎች መብት መከበር የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሆነም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት አስመልክቶ ያደረገውን የምርምራ ውጤትና ምክረ ሀሳብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን በማሳያነት ጠቅሷል።

ምክር ቤቱም የምርመራ ውጤቱንና ምክረ ሀሳቡን በመርመር ሪፖርቱን መቀበሉና ውሳኔዎች ማሳለፉ የዴሞክራሲያዊ ተቋማቱ ለህግ የበላይነት መረጋገጥና ለዜጎች መብት መከበር እያከናወኑ ያለውን ስራ የሚያሳይ ነው ብሏል።

ገዥው ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጀመሩት ውይይትም ለዴሞክራሲ ዕድገት የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ነው መግለጫው የጠቀሰው።

የዴሞክራሲ ተቋማቱ የጀመሯቸው ስራዎች የተሀድሶ እንቅስቃሴውን በማገዝ መንግስት ለህግ የበላይነት መከበርና ለዜጎቹ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ መጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳኩ እንደሆነም ፅህፈት ቤቱ አስታውቋል።

ተቋማቱ የጀመሩትን መሰል እንቅስቃሴ የሚያበረታታ መሆኑንና በቀጣይም ይህን ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አሳስቧል።