በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተይዘው የነበሩ 108 ሰዎች ተለቀቁ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተይዘው የነበሩ 108 ሰዎች የተሃድሶ ሥልጠና ከተሠጣቸው በኋላ  መለቀቃቸውን የክልሉ  መንግሥት አስታወቀ ።

በክልሉ በጥፋት  ሥራ ላይ  ተሳትፈዋል ተብለው የተያዙና በተሃድሶ ሥልጠናው የተካተቱ ሰዎች በቀጣይ ለፀረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሥልጠናው ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን  ገልፀዋል፡፡

108 የሚሆኑት  ሠልጣኞች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለ18 ቀናት ያህል በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፖሊስ ማሠልጠኛ ተቋም የተሠጣቸውን ትምህርት ካጠናቀቁ በኋላ ነው መለቀቃቸው ተመልክቷል ።

የሥልጠናውን መጠናቀቅ አስመልክቶ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አምባሳደር ምስጋና አድማሱ ሠልጣኞች ያገኙትን ግንዛቤ ተጠቅመው የሀገራቸውን ሠላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የሚፈልጉ አካላትን በመታገል የዜግነት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የተጀመረውን የልማት ጉዞ በማፋጠን የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሚደረገው ትግል ላይም ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን የድርሻቸውን እንዲያበረክቱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ (ምንጭ :ኢዜአ)