ዶክተር መረራ ጉዲና በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል መቃወሚያ አቀረቡ

ዶክተር መረራ ጉዲና በተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ላይ 11 ገጽ ያለው የክስ መቃወሚያ አቀረቡ።

የክስ መቃወሚያው የቀረበው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ነው።

በምድብ ችሎቱ ዛሬ በቀረበው የክስ መቃወሚያ በዋናነት ዶክተር መረራ“ ክሴ ከእነ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እና ጃዋር መሀመድ ጋር አብሮ ሊታይ አይገባም፤ የእኔ የህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ መንበርነት ከእነሱ አላማና አፈጻጸም ጋር የማይገናኝ በመሆኑ ሊነጠል ይገባል“ ይላል።

“ቤልጂየም ብራስልስ ለህዝባዊ ስራ ነው የሄድኩት፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቁጥር 11/2009 ዓ.ም መሰረት ኮማንድ ፖስቱ ያወጣው የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያ አንቀጽ 2/1 ስር የተመለከተውን ተላልፏል የተባለውን እቃወማለሁ“ ሲሉ በመቃወሚያቸው ጠቅሰዋል።

“በ2008 እና 2009 ዓ.ም በአማራና በኦሮሚያ ክልል ለተከሰተው ሁከት እና አለመረጋጋት እኔ ልጠየቅ አይገባም“ ሲሉም ተቃውሞዋቸውን አቅርበዋል።

“የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ተብሎ በሚጠራው ሚዲያ ላይ ስለ ኢሬቻም ሆነ የሁከት ጥሪ በሚመለከት ቃለ ምልልስ አላደረኩም“ ሲሉም የቀረበባቸውን ክስ ተቋውመዋል።

በአጠቃላይ በክሱ የወንጀል ስነስርአት ህግ ቁጥረ 111፣ 112 እና 130 አንቀጾች ዝርዝር ነገሮች ይቀሩታል በማለት በ11 ገጽ አያይዘው አቅርበዋል።

መቃወሚያውን የሰማው ፍርድ ቤትም መቃወሚያው ላይ የአቃቤ ህግ አስተያየትን ለመስማት ለሚያዚያ 26 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።