ምክር ቤቱ የህዝብ ውክልናን ከመወጣት አንጻር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ ገለፀ፡፡

ምክር ቤቶች የህዝብ ውክልናን ከመወጣት አንጻር እየተጫወቱ ያለው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ  ገለጹ ፡፡

የክልሉ ምክር ቤት የተገልጋዮችና የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል፡፡

ምክር ቤቱ የሚያከናውናቸውን እንቅስቃሴዎች ለህዝቡ ለማሳወቅና ግልጽነትን ለመፍጠር የህዝብ ግንኙነት ስራዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ወ/ሮ ህይወት ሃይሉ ገልፀዋል፡፡
ምክር ቤቱ የህዝቡን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት የሚያረጋግጡ በክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ፋይዳ ያላቸውን ህጎች በማውጣት እና በመገምገም ወደታች የሚወርዱበት አግባብ መኖሩንም  ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት ላይ ውይይት በማድረግ በተለይ በአስፈጻሚውና በህግ ተርጓሚው አካላት በምክር ቤቱ የጸደቁ ዕቅዶች፣ ህጎችና አዋጆች የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የጀመርነውን የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እና የዴሞክራሲ ስርኣት ግንባታችንን ዕውን ከማድረግ አንጻር እየተጫወቱ ያሉት ሚና ምን እንደሚመመስል የሚረጋገጥበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ የ2009 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት ዋና ዋና ተግባራት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በምክር ቤቱ የሚቀርቡ የአቤቱታና ጥቆማ ስራዎች፣ የህዝብ አስተያየት መስጫ መድረኮችን ማካሄድ፣ ድጋፋዊ ክትትል አፈጻጸም ማከናወን እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት በበጀት አመቱ የተከናወኑ ተግባራትም በሪፖርቱ ቀርቧል፡፡

የሴት የምክር ቤት አባላት አቅም በመገንባት የህዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግና በህግ አወጣጥ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ ላይ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንዲችሉ መደረጉም በሪፖርቱ ላይ ከቀረበው መረዳት ተችሏል፡፡

በዕለቱ በቀረበው የዘጠኝ ወራት አፈጻጻም ላይ የተገኙት ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎችን ተነስተው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ከመድረኩ በተሰጠ ማጠቃለያ መጠናቀቁም ታዉቐል፡፡