አመጽ የሚያስነሱ ሙዚቃና ግጥሞችን ዩ ቲ ዩብ ላይ አስጭነዋል የተባሉ ግለሰቦች ተከሰሱ

በጋዜጠኝነት ሙያ ተሰማርተው ሁከትና አመጽ የሚያስነሱ ዜና፣ ግጥምና ሙዚቃ በማዘጋጀት ዩ ቲ ዩብ ላይ እንዲጫን አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች ላይ ከስ ተመሰረተ።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ስለ ሃገሪቱ ፖለቲካ ቃለ መጠይቅ በማድረግ ዜናዎችን፣ ግጥሞችንና ሙዚቃዎችን፥ ከኦነግ ባንዲራና ወታደሮች ጋር በማቀናበር እና ወደ አውስትራሊያ በመላክ ዩ ቲ ዩብ ላይ እንዲጫን አድርገዋል በሚል ነው ክስ የቀረበባቸው።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው በ1ኛ ተጠርጣሪ ኦሊያድ በቀለና በኢፋ ገመቹ አስተባባሪነት፥ በሞይቡሊ ምስጋኑ፣ በቀነኒ ታምሩ፣ በሃይሉ ነጮ፣ በሴና ሰለሞን እና ኤልያስ ክፍሉ አዘጋጅነትና አንባቢነት ድርጊቱ ተፈጽሟል።

ተጠርጣሪዎቹ ከ2008 እስከ የካቲት ወር 2009 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባና በቡራዩ አካባቢ ቤት ተከራይተው ወንጀሉን መፈጸማቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህም የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ስለ ሃገሪቱ ፖለቲካ ቃለ መጠይቅ በማድረግ፥ ሁከትና አመጽ የሚያስነሱ ዜናዎችን በሳምንት ሁለት ጊዜ በኦሮምኛ በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅተው በድምጽ በመቅረጽ ማሰራጨታቸውም በክስ መዝገቡ ሰፍሯል።

ከዚህ ባለፈም ግጥሞችን በኦሮምኛ ቋንቋ በማዘጋጀት እና ሙዚቃዎችን ከኦነግ ባንዲራና ወታደሮች ምስል ጋር በማቀናበር አውስትራሊያ ለሚገኝ የኦነግ የሽብር ቡድን አመራር በመላክ ዩ ቲ ዩብ ላይ በማስጫን እንዲሰራጭ አስደርገዋል ሲል አቃቢ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

በዚህም መሰረት ከሳሽ አቃቢ ህግ ተጠርጣሪዎቹ ላይ የሽብር ተግባር በማሴር፣ ማዘጋጀትና ማነሳሳት ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ በነገው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19 ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ የሚነበብላቸው ይሆናል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።