ህብረቱ ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊና ለቀዳማዊ ኃይለስላሴ ሐውልት ለማቆም ወሰነ

የአፍሪካ ህብረት ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ እና ለቀዳማዊ  ኃይለስላሴ  መታሰቢያ ሃውልት እንዲቆምላቸው ወሰነ።

የአፍሪካ ህብረት የ29ኛው የመሪዎች ጉባኤ ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ እንዲሆን መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔው በ29ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ መዝጊያ ላይ ስነ ስርዓት ላይ የተላለፈ ነው።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ህብረቱ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከአፍሪካ አንድነት ድርጀት ምስረታ ጀምሮ ለአፍሪካ ህብረት ላበረከተቸው አስተዋጽኦ እውቅና ሰጥቷል።

ከዚህ ባለፈም ህብረቱ ለቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካውያንን ድምጽ በማሰማት ላበረከቱት አስተዋጽኦም የክብር መዘክር መስጠቱን አስታውቀዋል ፡፡

የአፍሪካ ህብረት የ29ኛው የመሪዎች ጉባኤ ለታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ መታሰቢያ እንዲሆን መወሰኑን አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገልጸዋል ።

በተጨማሪም የቀድሞው የኢትዮጵያ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታና እድገት ላበረከቱት አስተዋጽኦም የክብር መዘክር መስጠቱንም ገልጸዋል።

ለአፍሪካ አጀንዳዎች ቅድሚያ የምትሰጠውን ኢትዮጵያንና የቀድሞ መሪዎቿ በህብረቱ ለሰሩት ስራና ላበረከቱት አስተዋጽኦ፤ ከህብረቱ ለተሰጠው እውቅናና ክብርም በኢፌዴሪ መንግስት ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሳዑዲ ዓረቢያ ያለ ስራ እና መኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ዜጎችን የማስመለስ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አንስተዋል።

መንግስት በሳዑዲ ያለመኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን ጥረትም አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ።

በህጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ የሚያመሩ ዜጎች መብታቸውና ነጻነታቸው ተከብሮ ይሰሩ ዘንድ ለሳዑዲ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ የሚረዳና የዜጎችን ደህንነት የሚያስጠብቅ የጋራ ስምምነት ከሳዑዲ ጋር መፈረሙንም አስረድተዋል።

መንግስት ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ አጋርነት፤ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ምስረታ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ የደረሰችበትን አቋምም ለጋዜጠኞቹ ገልጸዋል።

በመግለጫቸው በህብረቱ የቀረበውንና ከአባል ሃገራት ያለ ቀረጥ የሚገቡ ምርቶችን መጠን፤ ኢትዮጵያ ከራሷ አንጻር በመገምገም እንዳልተቀበለችው አስረድተዋል።

ለዚህም በህብረቱ የቀረበውንና ሃገራት 90 በመቶ ወደ ሃገራቸው የሚገቡ የአባል ሃገራት ምርቶች ላይ ቀረጥ እንዳይጥሉ የቀረበውን እቅድ ከፖሊሲዋ አንጻር በመቃኘት 85 በመቶ ምርቶችን ያለ ቀረጥ ለማስገባት የያዘቸው አቋም በሃገራት ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቁመዋል።

ይህም የተጠቀሰው የምርት መጠን ያለቀረጥ ወደ ሃገር ውስጥ ቢገባ ካለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ አንጻር ታይቶ የተወሰደ እና ከሃገራቱ ጋር የሚሰራበት መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

በህብረቱ የመሪዎች የመዝጊያ ስብሰባ ላይ ህብረቱ፤ የአፍሪካን አጀንዳዎች ከመወሰን ባለፈ ማስፈጸምና ለተግባራዊነቱ ይሰራ ዘንድ የቀረበው የሪፎርም ማሻሻያ ተቀባይነት ማግኘቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻርም መደበኛ እና መደበኛ ያልሆነ በሚል በተለያየ ወቅት ሁለት የህብረቱ ስብሰባዎች እንዲካሄዱም ተወስኗል።

በዚህም የመሪዎቹ ዋና ስብሰባ የሆነው መደበኛ ስብሰባ ጥር ወር ላይ ተካሂዶ፤ የተላለፉ ውሳኔዎችን የሚገመግመው መደበኛ ያልሆነው ስብሰባ ደግሞ ሐምሌ ወር ላይ የሚካሄድ ይሆናል።

ከዚህ በኋላ የሚደረጉ የህብረቱ የመሪዎች ስብሰባም፤ በተመረጡ፣ ለአህጉሪቱ ይበጃሉ በተባሉ እና ተፈጻሚ በሚሆኑ አጀንዳዎች ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ ተወስኗልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ከዚህ አንጻርም የዛሬው የመሪዎች መዝጊያ ጉባኤ ለወጣቶች ቅድሚያ በመስጠት፣ በአህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም የተባበረችና የተዋሃደች አፍሪካን ለመፍጠር በሚያስችሉ አቅጣጫዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መምከሩን ነው በመግለጫቸው ያነሱት።

የተዋሃደች አፍሪካን ከመፍጠር አኳያም ከመሰረት ልማት ባለፈ አህጉሪቱን በንግድ የማስተሳሰሩ ጉዳይ ዋና አጀንዳ እንደነበርም አስታውቀዋል።

ከጅቡቲና ኤርትራ ወቅታዊ ፍጥጫ ጋር ተያይዞም የአፍሪከ ህብረት በራሱ ሰላም አስከባሪ ሃይል በማስፈር ጉዳዩን በራሱ እንዲፈታ ተወስኗል።

ከአፍሪካ ህብረት የገንዘብ ምንጭ ጋር በተያያዘ ባለፈው ታህሳስ ወር የተላለፈውና ሃገራት ከሚያገኙት ገቢ 0 ነጥብ 2 በመቶውን ለህብረቱ እንዲያስገቡ የተወሰነውን ውሳኔ አፈጻጸምም በመግለጫቸው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔው እስካሁን በ16 ሃገራት ብቻ እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጉዳዩ በሃገራቱ ፓርላማ አለመቅረቡና ሃገራቱ ከአለም የንግድ ድርጀት ጋር ያላቸው አሰራር እንቅፋት መሆኑን ነው አስታውሰዋል።

በቀጣይም ሃገራቱ ከአለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ጋር ያላቸውን አሰራር በመፈተሽ የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡንም አስታውቀዋል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።