ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዚዳንትና ከሌሎች  መሪዎች ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በመዲናዋ ከሚገኙት የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የፍልስጤም ራስ ገዝ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጋር ተወያይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መሀሙድ አባስ ጋር ባደረጉት ውይይትም በአገራቱ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ኢትዮጵያ የእስራኤልና ፍልስጤም አለመግባባት በሠላም እንዲፈታ ፍላጎት እንዳላትና ለሠላማዊ መፍትሄ ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ማረጋጣቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶማሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን አሊ ካይር ጋርም ዝግ ውይይት አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱዳኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሳቡ ሙሃመድ አብዱልራህማን ጋር ባደረጉት ውይይት የአገራቱ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዑመር ሀሰን አልበሽር ከወራት በፊት ኢትዮጵያን ከጎበኙ በኋላ የአገራቱ ጉርብትና የበለጠ የሚያጠናክር እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል የቴክኒክ ትብብር መድረክ መፍጠራቸውን ጠቅሰው፤ የኢትዮ-ሱዳን የቴክኒክ ትብብር ስብሰባ በቀጣዩ ወር በሱዳን ካርቱም እንደሚካሄድም ነው ያስታወቁት።

የደቡብ ሱዳን የሠላም ሁኔታ እንዲሻሻል ኢትዮጵያና ሱዳን የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የተስማሙት።

በሱዳን ወደብ አጠቃቀምና በትራንስፖርት ስምሪት በትብብር መስራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል (ኢዜአ) ።