ካናዳና ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የየአገሮቹ አምባሳደሮች ለኢዜአ እንዳሉት ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ዕድል ተጠቅመው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የተጀመሩ የድጋፍ ሥራዎችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደሮቹ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሜን አሜሪካ እና ስካንድቪዲያን አገሮች ጋር ግንኙነቷን ከጀመረች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረች ሲሆን በእርዳታ ላይ ብቻ ተመስርቶ የቆየው ግንኙነት ወደ ንግድና ኢንቨሰትመንት ትብብር እየተቀረ መጥቷል።
በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር አንድሪያስ ጋርደር ኢትዮጵያና ኖርዌይ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው በማስታወስ የኖርዌይ መንግስት ትኩረት በማድረግ ከሚደግፋቸው 12 አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ገልጸዋል።
በትምህርት መስክና ሕገ-ወጥ ስደትን ለማስቀረት የኖርዌይ መንግስት ኢትዮጵያን የመደገፍ ተግባሩ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሰብአዊ መብት አጠባበቅ፤ በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲ ግንባታው ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ከምትሰራቸው ዘርፎች መካከል ተጨማሪ አጀንዳዎች ናቸው።
"በትምህርት ጉዳዮች ላይ የጀመርነውን ድጋፋችንን አጠናክረን መቀጠል እንፈልጋለን" ያሉት አምባሳደሩ የኖርዌይ ባለኃብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥረት እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
ከዚህ በፊት የአገሪቱ ንጉሥ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የተፈራረሟቸው ስምምነቶችን በተለይም የአፋር የፖታሽ ማዕድን ሥራና ሌሎችም ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ክትትል ይደረጋል ብለዋል።
“ከዚህ ቀደም 'ያራ' የተሰኘው የኖርዌይ ማዕድን ፈላጊ ኩባንያ ከኢትዮጵያ የማዕድን ሚኒስቴር ጋር በአፋር ክልል ማዕድን ለማውጣት ውል ተፈራርሟል። በሌሎች ዘርፎችም ብዙ ፍላጎቶች አሉ፣ እነዚህን አጠናክረን እንቀጥላልን" ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ መዳረሻዎች ያሉት መሆኑና በአገሪቷም ትልቅ ገበያ መኖሩ ባለኃብቶቹ በቀላሉ በንግዱ ዘርፍ እንዲሳተፉ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል አምባሳደሩ።
ኢትዮጵያና ኖርዌይ በትብብር ከሚሰሩባቸው በርካታ መስኮች መካከል ሠላምና ፀጥታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሕገ-ወጥ ስደትን መቀነስ፣ ዘላቂ ልማትን ማምጣት፣ ፆታዊ እኩልነት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ፊሊፕ ባከር በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያና ካናዳ መካከል የቆየ ግንኙነት እንዳለ ገልጸው፤ በተለይ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ሴቶችን ማብቃትና ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ካናዳ እንደምትደግፍ ገልጸዋል።
”በኢትዮጵያ ጥሩ የምግብ ዋስትና መርሃ-ግብር ተቀርጿል፤ እኛም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸውን ዜጎች ለመለወጥ በሚደረገው ጥረት ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። ሴቶችን ማብቃት፣ በሠላምና ፀጥታ ዙሪያም በጋራ የምንሰራው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
የካናዳ ባለኃብቶች በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደር ባከር፤ “በተለይ በግብርና ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ ትኩረት ይደረጋል” ነው ያሉት።
የካናዳ ኩባንያዎችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉና የሁለቱን አገሮች የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ካናዳ በዓለም አቀፉ የልማት ትብብር ኢትዮጵያን ከሚደግፉ አገሮች መካከል በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በኢትዮጵያ የመሠረተ ልማት አውታሮች በአሁኑ ወቅት እየተስፋፉ መምጣታቸው፤ አርሶ አደሩ በቀጥታ ምርቶቹን ለገበያ እንዲያቀርብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል ያሉት አምባሳደሮቹ፤ በአገሪቱ ምቹ የገበያ ዕድል እንዳለ መታዘባቸውን ተናግረዋል።
—END—