የትግራይ ክልል ምክርቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እንደሚጀምር አስታወቀ

የትግራይ ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን ነገ ማካሄድ እንደሚጀምር የምክር ቤቱ ሕዝብ ግንኙነትና ኮንፍረንስ አገልግሎት ዳሬክቶሬት አስታወቀ፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ታረቀ እንደገለጹት፤ምክር ቤቱ ጉባኤውን የሚያካሂደው ከጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ነው።

በጉባኤውም የክልሉ ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚን የስድስት ወራት ሪፖርት እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤትና ዋና ኦዲተር ሪፖርትን አዳምጦ ከተወያየ በኋላ ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ሙሉጌታ አመልከተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ  በጉባኤው አዳዲስ አዋጆች እንደሚፀድቁ ይጠበቃል ነው ያሉት።

ለምክር ቤቱ ከሚቀርቡ ስድስት አዋጆች መካከል የቴምብር ቀረጥ አከፋፈል ግልጽና ፍትሀዊ ለማድረግ የቀረበ አዋጅ እንደሚገኝበት አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ መሬት ለሌላቸው ወጣቶችና ለአርሶ አደሮች የግብርና ፓኬጅ ማስፈጸሚያ ከደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ የ450 ሚሊየን ብር የብድር ዋስትና ለመስጠት የቀረበ አዋጅን ተመለክቶ እንደሚያጸድቅም ነው የጠቆሙት፡፡

ለመጪው የመኸር ወቅት አገልግሎት የሚውል የአፈር ማዳበሪያ መግዣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ975 ሚሊየን ብር የብድር ዋስትና ለመስጠት የቀረበ አዋጅም ለምክር ቤቱ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሏል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው በዳኞች ሹመትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ እንደሚያፀድቅ አቶ ሙሉጌታ ገልፀዋል።(ኢዜአ)