በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮ-አውሮፓ ህብረት የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል

ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የኢትዮአውሮፓ ህብረት የምክክር መድረክ ትናንት ተጠናቋል።

በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል በኢኮኖሚ ልማት፤ በማህበራዊ፣ በኢንቨስትመንትና በንግድ ላይ ያተኮረው ይህ ምክክር በስኬት መጠናቀቁን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ የተመራው የምክክር መድረኩ ከአውሮፓ ህብረት የስራ ሃላፊዎች ጋር በአየር ለውጥ፣ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጉም ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታው ባደረጉት ንግግር፣ውይይቱ ሀገራችን ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ጠቃሚመሆኑን ገልጸዋል።

ምክክሩ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚጠቅምም ተናግረዋል።

በውይይቱ፣ የኢትዮአውሮፓ ህብረት የምክክር መድረክ ሁለቱም ወገኖች ስምምነት በተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ የትግበራ ነጥቦች እንዲዘጋጁ ስምምነት ላይ መደረሱም ተጠቁሟል።

ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረገውን ዘርፈ ብዙ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደዚህ አይነት የምክክር መድረኮች ለወደፊቱ እንዲዘጋጁ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱም የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያመለክታል።

የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ህብረት መካከል .. 2016 . የተፈረመው የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት አካል ነው።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት 43 ዓመታት የቆየ የልማት ትብብር አላቸው።

የአውሮፓ ህብረት 300 የሚደርሱ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ 100 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አውሮፓ የመጀመሪያውን ዲፕሎማት የላከችው ፖርቹጋል ሊዝበን ከተማ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1514 ነው።(ኢዜአ)