በአዳማ እሁድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ ይካሄዳል

ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዓብይ አሕመድ ላስመዘገቧቸው የአመራር ውጤቶቸ ድጋፍ ለመስጠት በአዳማ ከተማ እሁድ የሚካሄደውን የድጋፍ ሰልፍ ለማከናወን ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውን የዝግጅት ኮሚቴው ገለፀ፡፡

የዝግጅቱ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ባሌማ ለዋልታ እንደገለጹት በዕለቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር ሰኞ 16፣ 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ማውገዝ፣ የደም ልገሳ ለማከወናንና በቦንብ ፍንዳታው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡

የድጋፍ ሰልፉን በሰላም እንዲጠናቀቅ ከጸጥታ ኃይሎች፣ ከወጣቶች፣ የሐይማኖት ተቋማትና ሌሎች አካላት ጋር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን አቶ ተስፋዬ አክለው ገልጸዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ዝግጅት ወጣቶችና የንግዱ ማህበረሰቡ አካላት ከፍተኛውን ድርሻ እንዳበረከቱ የአብይ ከኮሚቴው የፋይናንስ ጸሐፊ አቶ ዮሴፍ ኃይለጊዮርጊስ ተናግረዋል፡፡ ወጣቶችን ከሱስ ነፃ ማድረግ፣ የሥራ ፈጠራን ማዳበር፣ ወደ አስመራ የሚደረግን ጉዞ ማጠናከር ከድጋፍ ሰልፉ ጎንለጎን የሚከናኑ ተግባራት እንደሆኑም ታውቀዋል፡፡

የአዳማና ከተማ እና የምስራቅ ሸዋ አካባቢ ነዋሪዎች ከጠዋቱ 1፡00 ጀምሮ በድገፍ ሰልፉ ላይ እንደሚሳተፉና ቁጥራቸው እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚደርሱ ዜጎች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

“ለውጥን እናስቀጥል ዴሞክራሲን እናበርታ!” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ የድጋፍ ሰልፎች በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እንደተካሄደ ይታወሳል፡፡