የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ተጀመረ

የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አምስተኛ ዘመን 12ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተጀምረዋል።

ጉባኤው የተጀመረው በበጀት ዓመቱ የምክር ቤቱን የስራ እቅድና አፈጻጸም ሪፖርትን በማቅረብ ነው።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት፣በየደረጃው በሚገኙ ምክር ቤቶችና የስራ አስፈጻሚ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የተጠያቂነትና የግልጸኝነት አሰራር እየተሻሻለ መጥቷል።

“በበጀት ዓመቱ የኦዲት ግኝት፣ የክልሉ ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት ባካሄዱባቸው የክትትልና ቁጥጥር ስራዎች 60 በመቶ ያህሎቹ የአሰራር መሻሻሎች የታዩባቸው ሆነው ተገኝቷል” ብለዋል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር በዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚቀርበው ሪፖርት በማዳመጥ ይገመግማል።

እንዲሁም ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑት የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የዋና ኦዲተርና የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ዓመታዊ የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይም ጉባኤው ይመክራል።

በተጨማሪም የክልሉ ምክር ቤት እምነት ባጣባቸው ዳኞች ምትክ እንደሚሾም እና ለ2011 የስራ ዘመን ማስፈጸሚያ የሚውል የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል፡፡ (ኢዜአ)