በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መቋጨቱ እንዳስደሰታቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መቋጨቱ እንዳስደሰታቸው አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ አስመራ የልዑካን ቡድኑን መርተው በመሄድ ለብዙ አመታት ተራርቆ የኖሩትን ወንድማማች ህዝቦች እንዲስማሙና በዜጎቹ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር ማድረጋቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

ለዋልታ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ሃምሳ አለቃ ሞገስ ሞኮንን ከዚህ በፊት በነበረው የድንበር ግጭት የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች አብረው መኖር እያማራቸው ለብዙ አመታት ተለያይተው የቆዩ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት ግን ሰላም ተፈጥሮ የሁለቱ ሀገራት ባንድራ ባንድ ላይ ተውለብልቦ ማየት ባጣም ደስ እንዳሰኛቸው ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ፋሲል ንጉሴ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በፊት የገቡትን ቃል በተግባር እያሳዩ መሆናቸውን ገልጸው የኤርትራ ህዝቦች አቀባበልም በህዝቦች ዘንድ ያለውን አብሮ የመኖር ፍላጎት እንደሚያሳይና በበኩሉ ያልጠበቀው ነገር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የሁለቱ ሀገር ዜጎች ተዋደውና ተፋቅረው የሚመላለሱበትና በጋራ የሚሰሩት መንገድ የምከፍት እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎቹ አንስተዋል፡፡

ነዋሪዎቹ የሁለቱ ሀገራት ስምምነት የምስማሙበትና የምፈልጉት በመሆኑ በደስታ እንደምደግፉም ገልጸዋል፡፡