የአማራ ክልል ምክር ቤት 10ኛ መደበኛ ጉባኤን በባህር ዳር እየተካሄደ ነው

የአማራ ብሄራዊ ክልል ምክር ቤት 5ኛ ዙር፣ 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን፣ 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በባህር ዳር እየተካሄደ ይገኛል።

ጉባኤው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ቆይታ የሚያደርግ ሲሆን በቆይታው በ2010 ዓ.ም በጀት አፈጻጸም ሪፖርት እንዲሁም በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የ2010 በጀት የ11 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አቅርቦ ይወያያል።

የክልሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በ2009/2010 በጀት ዓመት ኦዲት የተደረገ የ2009 በጀት ሂሳብ ኦዲት ውጤት ሪፖርትም ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ የምክር ቤቱ አባላት የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መስራት አለባቸው ብለዋል።

አባላቱ በየአካባቢያቸው ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙም ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቅሰው የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከርም ምክር ቤቱ ሀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ምክር ቤቱ የተለያዩ ዳኞች ሹመትም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። (የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት)