ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገለጸ

የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነገ አዲስ አበባ ይገባሉ፡፡

የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ግብዣ መሰረት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተመራ ከፍተኛ የኤርትራ የልዑካን ቡድን የሁለት ቀናት ጉብኝት ለማድረግ ነገ አዲስ አበባ ይገባል፡፡

ፕሬዝዳንቱ በቆይታቸው በዶክተር አብይ አህመድ ከተመራ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር የሁለቱ አገሮችን ታሪካዊ ወዳጅነት ለማጠናከር በቅርብ የተጀመረው ጥረት በሚጠናክርበት ሁኔታ ላይ ይመክራሉ፡፡

ዶክተር አብይ አህመድ በአስመራ ጉብኝታቸው ወቅት የተፈረመው የጋራ መግለጫ የሚያከብርና የሚያወድስ ፕሮግራም እንደሚካሄድም ተገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተመራው የልዑካን ቡድን ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ደማቅ አቀባበል ያደረጉ ሲሆን የልዑካን ቡድኑ አዲስ አበባ ከገባ ጊዜ ጀምሮ የተለየ የወዳጅነት መስተንግዶ ለማድረግ በመንግስት አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ 

በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለሚመራው ወንድም ለሆነው የኤርትራ የልዑካን ቡድን ህዝብ ደማቅ አቀባበል እንዲያደርግ ተጋብዟል፡፡

ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገሮችና ህዝቦች መካከል የተጀመረውን ጠንካራ ሁለንተናዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተወሰደ መልካም እርምጃ ነው፡፡

በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተደረሰውን አዲስ የሠላም እርምጃ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚቀጥለው ሳምንት ከ20 ዓመት በኃላ የመጀመሪያውን በረራውን እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡